በመደመር ፍልስፍና የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ መስራትን መርህ ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር ፍልስፍና የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ መስራትን መርህ ያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ለጋራ ሀገራዊ ዓላማ በጋራ መስራትን መርህ ያደረገ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነት አለባቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ እምነት ካጡ እንደ ፓርቲም እንደ ፖለቲካም ይከስራሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ ለጋራ ዓላማ በጋራ መስራትን መርህ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አካባቢዎች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በመሰባሰብ የፈጠሩት ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ህዝብ ኃላፊነት የተረከበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጋ አባላት ያሉት ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ ነው ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 50 በመቶ መቀመጫ ማግኘት ያልቻሉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በካቢኔ እንዲካተቱ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ሕዝብን ማገልገል ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተው፤ የቴሌኮምና የባንክ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ውጤታማ የኢኮኖሚ ሪፎርም አድርገናል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሕዝቡን በማስተባበር ከነበረበት አንስቶ በማጠናቀቅ፤ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር እንዲጠቅም መደረጉን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሕዝቡን በማስተባበር 56 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለአፈርና ውሀ ጥበቃ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ገንቢ ሚና እየተወጣን ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ የፈለገውን ቢመርጥም የብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖራቸው እንደማይገባ ገልጸው፤ ለወጣት መሪዎች ዕድል መስጠት ይገባልም ብለዋል።