ብልፅግና ፓርቲ በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት ከመስራት ባሻገር የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ተጠያቂነትን እያሰፈነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት ከመስራት ባሻገር የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ተጠያቂነትን እያሰፈነ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2019 (ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት ከመስራት ባሻገር አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት፣ ድክመትና ጥንካሬውን በመለየት ተጠያቂነትን እያሰፈነ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለአፍሪካውያን አንድነትና የጋራ ርዕይ የሚመከርበት ነው።
አፍሪካ ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብልፅግና ለማረጋገጥ የተሰባሰቡበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ ስብሰባው እየተካሄደበት ያለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ነፃነት የተዋደቁበት መታሰቢያ ነው ብለዋል።
የእዚህ ዘመን ትውልድ የአፍሪካን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ምርታማነቱን ወደ ማሳደግ ሊቀይረው እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካታች የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ከምርጫ ጊዜ ባለፈ ዘወትር የሕዝብን ህይወት በሚቀይሩ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የመደመር ሀገር በቀል ፍልስፍና ለጋራ ዓላማና በአንድነት በጋራ መስራት ነው ያሉት አቶ አደም፤ ብልፅግና ፓርቲ በቅንጅት ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ዕውን የማድረግ ርዕይ ማንገቡን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጋ አባላት ያሉት ግዙፍ ባለ ርዕይ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው፤ ፍትህ፣ እኩልነትና ብዝሀነት ቁልፍ እሴቶቹ መሆናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፓርቲ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት፣ ድክመትና ጥንካሬውን በመለየት ተጠያቂነትን አስፍኗል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሚራው መንግሥት በህዝብ ጉዳዮች ላይ በትኩረት በመስራት በዜጎች ዘንድ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ገልጸው፤ በመደመር ፍልስፍና አካታችነትና የተቀናጀ አቅም መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ፍትሀዊ የውድድር መድረክ በመፍጠር በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለጋራ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ በጋራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው አፍሪካውያን በመደመር መንፈስ ውጤታማ ትብብር ለመፍጠር የሚመክሩበት መድረክ መሆን አለበትም ብለዋል።