ዓለም አቀፍ ዜናዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ዜናዎች
አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ይኖርብናል - የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ
Apr 15, 2025 301
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አቅም መገንባት ይኖርብናል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት 24ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል። ምክር ቤቱ በስብሰባው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአንድ አባል ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ህግ አማካሪ አደረጃጀት (AUCIL) አንድ አባል እንዲሁም የአፍሪካ የህዋ ምክር ቤት (AfSC) አንድ አባል ምርጫ ይከናወናል ። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን እና የትምህርት ፣ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር የምርጫ ሂደት አስመልክቶ የተዘጋጀ ረቂቅ ሪፖርት ያዳምጣል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአፍሪካ አህጉር በርካታ ውስብስብ ችግሮች እየገጠሙት ይገኛል። የአንዳንድ እርዳታ ሰጭ ተቋማት ድጋፍ መቋረጥ በጤናና በምግብ ዋስትና ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የመሳሰሉ ዘዴዎችን ለመተግበር በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ቴቴ አንቶኒዮ በበኩላቸው፤ ሰላም እና መረጋጋት ለእድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አህጉራዊ ተቋማት የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠቃሚ ግብዓት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህም የውሳኔ ሰጭውን አካል መፍትሄ የሚፈለግ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪካ ህብረት እነዚህን ተግዳሮቶች በጥበብ እና አርቆ አስተዋይ አመራር በመምራት ረገድ ንቁ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ናቸው። የ2063 አጀንዳን ራዕይ ለማሳካትና የበለፀገች አህጉርን ለመፍጠር አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ቀልጣፋ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብስባ እየተካሄደ ያለው በየካቲት 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።
ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ተጀመረ
Apr 7, 2025 387
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄድ ጀምሯል። ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው “ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እርምጃዎችን በፋይናንስ መደገፍ ለአፍሪካ ዘላቂ አረንጓዴ እድገት እና ልማት፤ የፍትህ ጉዳይ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው። በመክፈቻው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ፣ የህብረቱ አመራሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በአዘርባጃን ባኩ የተካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) የተላለፉ ውሳኔዎች በአፍሪካ ላይ የሚኖራቸውን አንድምታ በተመለከተ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው ያመለክታል። በኮፕ 29 ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አስመልክቶ ውሳኔ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ለአፍሪካ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አለመስጠታቸውን የገለጸው ህብረቱ በጉዳዩ ሀገራት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ገልጿል። በብራዚል ቤለም በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) የአፍሪካ የጋራ አቋም ምን መሆን አለበት? በሚለው ጉዳይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል። እ.አ.አ በ2024 አፍሪካን የተመለከቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች እና በ2025 በሚኖሩ አጀንዳዎች ላይም ምክክር ይደረጋል። በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ (CAHOSCC ) በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ይገመገማሉ። የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም ሌላኛው የውይይቱ አጀንዳ ናቸው። በንጹህ መጠጥ ውሃ እና በማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የዋሽ ፕሮጀክት (WASH) አፈጻጸም ለተሳታፊዎች ቀርቦ ምከረ ሀሳብ ይሰጥበታል። በስብሰባው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና የዘላቂ ልማት ግቦችን የተመለከተ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚጸድቅ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል። ስድስተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ውይይት እና የዘላቂ ልማት ግቦች ፎረም እስከ ነገ ይቆያል።
የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ሊገባ ነው
Mar 31, 2025 374
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካን የባህር እና የመጠጥ ውሃ ሀብቶች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከርን ያለመው የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ ተገለጸ። ስትራቴጂውን ለማፅደቅ የተዘጋጀ አውደ ጥናት ከነገ ጀምሮ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ይካሄዳል። ስብሰባውን ያዘጋጁት የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በጋራ በመተባበር ነው። የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ የአፍሪካን የባህር እና የመጠጥ ውሃ ሀብቶች የሀገራት እና የዘርፉ ተዋንያን ትብብርን ለማጠናከር ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ውይይት እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል። የስትራቴጂው ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ የክትትል ስርዓትና የድርጊት መርሃ ግብር ውይይት የሚደረግባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች ናቸው። የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ስትራቴጂውን ከብሄራዊ እቅዶቻቸው ጋር አጣጥመው በሚተገብሩበት ሁኔታ ላይም ይመክራሉ። የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂው ከአፍሪካ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ ከዘላቂ ልማት እና ዓለም አቀፍ ግቦች ጋር ያለው ትስስርም ውይይት ይደረግበታል። እ.አ.አ በ2023 በአሜሪካ ኒው ዮርክ የተፈረመው ዓለም አቀፍ የባህር ብዝሃ ህይወት ዘላቂ አጠቃቀም ስምምነት (BBNJ Agreement) የትግበራ አፈጻጸም ሌላው የአውደ ጥናቱ የመወያያ አጀንዳ ነው። የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ ጁን 2025 በፈረንሳይ ኒስ በሚካሄደው ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት የውቅያኖስ ኮንፍረንስ ላይ ይዘው የሚቀርቡትን የጋራ አቋም ይፋ እንደሚያደርጉም የህብረቱ መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ የውቅያኖስ አስተዳደር ስትራቴጂ ለማፅደቅ የሚደረገው አውደ ጥናት እስከ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
የአፍሪካ ህብረትና አሜሪካ በቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ ያላቸውን የጋራ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ
Mar 27, 2025 360
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ዙሪያ ያላቸውን የጋራ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ አምባሳደር ስቴፋን ሱሊቫን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል። ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት እና የአሜሪካ የቆየ ትብብር ማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን መለየት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ አጋርነት ለሶማሊያ የሰላም እና መረጋጋት ጥረቶች ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል። ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት በቁርጠኝነት መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ከአፍሪካ ህብረት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ 48 ሃገራት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል
Mar 25, 2025 301
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ እስካሁን 48 ሀገራት የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ ለትግበራው ቁርጠኛነታቸውን ማሳየታቸውን የአህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናው ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 የልማት ማዕቀፍ ከተያዙ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ስር ከሰደደ ድህነት እንደሚያላቅቅ ይጠበቃል። የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነትን እ.ኤ.አ. በ2018 በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ መፈረማቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያም ስምምነቱን በወቅቱ ከመፈረም ባለፈ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል መጋቢት 12/2011 ዓ.ም አፅድቃለች። ዋና ጸሐፊው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን 48 የአህጉሪቱ አባል ሀገራት አጽድቀውታል። እነዚህ ሀገራት ስምምነቱን ለመተግበር ያላቸውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳልጡ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎች እያዘጋጁ ነው ብለዋል። ከዚህም ባለፈ 19 አባል ሀገራት የቀረጥ መርሃ ግብር በማውጣት የንግድ ግብይት ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። አክለውም የአነስተኛና መካከለኛ አርሶ አደሮችን ምርት በማሰባሰብ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ ድርጅቶችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም የአፍሪ-ኢግዚም ባንክ ለነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የ750 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል። የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት በማረጋገጥ የህዝቧን ተጠቃሚነት ማጎልበት የህልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቀድሞ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዬሚ ኦሲንባጆ ናቸው። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በጠንካራ የፖለቲካ አመራር መተግበር የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል። ከአህጉራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት መካከል አንዱ የሆነው ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ፤ የአፍሪካን የወደፊት የኢኮኖሚ እጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑንም ተናግረዋል። የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ዕድገት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለስኬቱም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል። የአፍሪካን አህጉራዊ ውህደት ራዕይን እውን ለማድረግ እ.ኤ.አ በ1963 ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ለአብነትም የአፍሪካ መሪዎች እ.አ.አ በ2012 በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ 18ኛ መደበኛ ጉባኤ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና እንዲመሰረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም እ.ኤ.አ በ2015 ድርድሩን በይፋ በመጀመር በ2018 አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነቱ በይፋ ተፈርሟል። የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት 55 የአፍሪካ ሀገሮችን በአንድነት ያካተተ የነጻ ንግድ ስርዓት የፈጠረ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ስምምነት ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኛው እቃዎች ላይ በሂደት ታሪፍን ለማስወገድ፣ የአገልግሎት ንግድን በሂደት ክፍት ለማድረግ እና የንግድ መሰናክሎችን ለማስወገድ የተስማሙበትም ነው፡፡
ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ይሰራል - ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)
Mar 14, 2025 260
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገለጹ። ዋና ፀሐፊው ከወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር እና የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው 43ኛው የኢጋድ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ውጤቶች ላይ ያተኮረ ነበር። ዋና ጸሀፊው ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በውይይቱ በጉባዔው ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እና ኢጋድ ቀጣናዊ ፈተናዎችን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ላይ ከሊቀመንበሩ ጋር ሀሳቦች እንደተለዋወጡ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል። አስቸኳይ ጉባኤውን ተከትሎ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች አለመግባባቶችን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ኢጋድ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል አለባቸው
Feb 12, 2025 582
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ መሻሻል እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ። 46ኛው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት፤ አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም ብለዋል። አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳድረው ተፅዕኖ ጥቂት ቢሆንም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ገልጸዋል። በመሆኑም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ሪፎርም መደረግ አለባቸው ብለዋል። የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በመሰረታዊነት መቀየር እንዳለበትም ገልጸዋል። አፍሪካውያን አህጉራዊ ሀብታቸውን እሴት ጨምረው መጠቀም እንዲችሉ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በአህጉሪቱ ጥሬ ምርትን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ የመላክ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አፍሪካውያን ለደረሰባቸው ግፍና በደል ተገቢ የፍትሕ ካሳ ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል። ይህ ችግር የዓለም የንግድ ስርዓትን በማዛባት የአፍሪካውያንን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ተናግረዋል። አፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላት አሉታዊ ተፅዕኖ ውስን ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን አልዳነችም ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አፍሪካን የአህጉራዊ ጥቅል ምርቷን አምስት በመቶ እንደሚያሳጣት በመጥቀስ፣ በዓለም ዙሪያ ለኢንቨስትመንት ከሚመደበው ሀብት የአፍሪካ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ይሄ የአፍሪካን ጥቅም የሚጎዳ ኢፍትሃዊነት በቃህ ሊባል ይገባል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መሰረታዊ ሪፎርም ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቀድሞው ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
Jan 30, 2025 476
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በሙስና በመደለል ከግብፅ መንግስት ጉቦ የተቀበሉት አሜሪካዊው የቀድሞው የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የፍርድ ውሳኔውን ትናንት ማስተላለፉን የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ ዘግቧል። ችሎቱ ከዚህ ቀደም የ71 ዓመቱን የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል። የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል መክሰሳቸው ይታወቃል። ዐቃቤ ሕጉ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል። የቀድሞው ሴናተር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ በኒው ጄርሲ በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 የግብጽ ሰዎች እጅ ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ ጉቦ ተቀብለዋል። ይህም ሴናተሩ ራሳቸውን ለግብጽ መንግሥት ወኪል አድርገው በመቆም ሰርተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህም በዘረፋ፣ ጉቦ በመቀበል፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ በሴራ፣ ፍትህን በማደናቀፍና መሰል 16 ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገልጿል። በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም እንዲሁ። ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ በቤታቸው መገኘቱን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም በስፋት ዘግበውታል። የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል። በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል። እ.አ.አ በ2021 የ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው። በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበር ይታወቃል።
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣቷን ውሳኔ ማጤን አለባት - የአፍሪካ ህብረት
Jan 22, 2025 561
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣት ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቀዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት መፈለጓ እንዳሳዘናቸው ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል። ውሳኔውን መለስ ብሎ በማጤን በአባልነቷ ትቀጥላለች የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል። አሜሪካ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) መስረታ ላይ ቀደምት እና ጠንካራ ደጋፊ ነበረች ሲሉም በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፉን የህብረተሰብ ጤና ደህንነት እንደ አንድ የጋራ ጥቅም የማረጋገጥ ተልዕኮውን ለመወጣት በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ጥገኛ መሆኑን የገለፀው ህብረቱ፤ የድርጅቱ ቁልፍ መስራች አባል የሆነችው አሜሪካ ከተቋሙ የመውጣት ውሳኔዋን በድጋሚ እንድታጤነው ጠይቋል።
26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤን ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች - ግብርና ሚኒስቴር
Jan 15, 2025 509
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ልታስተናግድ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ በየዓመቱ በግንቦት ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሚካሄድ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ ደግሞ በየአህጉራቱ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ 25ኛው ጉባኤ እአአ በ2023 ቦትስዋና ያስተናገደች ሲሆን 26ኛውን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧንም አስታውቋል። ጉባኤው "የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ለጉባኤው መሳካት ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ዋናው ጽህፈት ቤት፣ የአፍሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውም ተገልጿል። የግብርና ሚኒስቴርም ግብረ-ሃይል በማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡ በጉባኤው ከየአፍካ ሀገራት የጤና ኃላፊዎችና ቋሚ ተወካዮች፣ ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት፣ በየአህጉሩ ያሉ የእንስሳት ጤና አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንደሚታደሙም ተጠቁሟል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነጻ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል። በጉባኤው በእንስሳት ጤናና ልማት፣ በምግብና ስነ-ምግብ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገኙና የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተሰሩ ያሉ እንደ ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና እና የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በስፋት ውይይት ይደረግባቸዋል፤ አቅጣጫዎች ይቀመጡበታል ሲሉም ተናግረዋል። የእንስሳት ጤና በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ለማምረት እንደሚረዳ፣ መቀንጨርን ከመከላከል አንጻር የእንስሳት ጤና ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለውም የምናይበት መድረክ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና በአህጉር ደረጃ ካሉ ሀገራት ጋር ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል። ሀገራት ያላቸውን የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂና ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያም በእንስሳት ጤና፣ መሰረተ ልማት እና ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለዓለም የምታስተዋውቅበት፣ ልምድ የምንጋራበት መድረክ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ከመቶ ዓመት የዘለለ የእንስሳት ጤና አገልግሎትና የምርምር ተቋማት፣ በእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ፣ ክትባትና መድሃኒት የሚያመርቱ፣ በእንስሳት ጤና የሰው ሃይል የሚያፈሩ ተቋማት መኖራቸው መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ብሎም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።
አፍሪካ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ማሳየት ችላለች
Jan 3, 2025 467
አዲስ አበባ፤ ታኅሳሥ 25/2017 (ኢዜአ) አፍሪካ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ማሳየቷ ተገለፀ። አሕጉሪቱ የወሰደቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ደግሞ ለተገኘው ጥንካሬ በምክንያት ተነስተዋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጡት ትንበያ እንዳመለከተው አፍሪካ በዓመቱ የ 3 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች። እንዲያም ሆኖ የዋጋ ግሽበት እና የብድር ዕዳ መጨመር ዋነኛ የሕጉሪቱ ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን የአፍሪካ ቢዝነስ ዘገባ አመልክቷል።
የአሜሪካ 39ኛ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው አረፉ
Dec 30, 2024 853
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 21/2017 (ኢዜአ)፡- የአሜሪካ 39ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻው ጊዜያቸው በፔሊንስ ጆርጂያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው “በቤተሰቦቻቸው ተከበው ነበር” ሲል ካርተር ሴንተር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካርተርን “ውድ ጓደኛ” እና “ልዩ መሪ” ሲሉ የተሰማቸውን ሀዘን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አሜሪካውያን ለቀድሞው ፕሬዝዳንት “የምስጋና እዳ አለባቸው” ብለዋል። የአሜሪካ መንግሥት የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ሥርዓተ ቀብር ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ አመልክቷል። የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ባለቤት ሮዛሊን ካርተር እ.ኤ.አ. በ2023 ወርሃ ኅዳር በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሁለቱ ጥንዶች ለ75 ዓመታት አብረው በትዳር አብረው ኖረዋል። ካርተር እ.ኤ.አ. ከ1977 እስከ 1981 አሜሪካን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ፕሬዝዳንት ካርተር እ.ኤ.አ. በ1980 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የካሊፎርኒያ ገዢ በነበሩት ሮናልድ ሬገን ሲሸነፉ የካርተር ማእከልን እ.ኤ.አ. በ1982 አቋቁመው ወደ በጎ አድራጎት ተግባር ተሰማርተው ነበር። የካርተር ማእከልም ከኢትዮጵያ ጋር በሽታን በከላከልና በመቆጣጠር፣ የምግብ ምርትን በማሳደግ፣ ግጭትን በማስወገድና በምርጫ ታዛቢነት በመሳተፍ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ነበረው።
ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሸፍኗል- ሚኒስቴሩ
Dec 24, 2024 703
ደሴ፤ ታኅሣሥ 15/2017 (ኢዜአ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል። ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ለማልማት እየተሰራ ይገኛል፡፡ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት በስንዴ ዘር መሸፈን እንደተቻለ ነው የተናገሩት። ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በበቂ መጠን እያቀረበ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ እስካሁን ከ120 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል። በክልሉ በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ጭምር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት አድርገናል -በጎ ፍቃደኞች
Dec 22, 2024 454
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን በጎ ፍቃደኞች ገለጹ። ኢትዮጵያ 38ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በብቃት ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋም ተገልጿል። በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ለማስተናገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዕጩና ነባር ዲፕሎማቶች እንዲሁም ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። የስልጠናው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለውን የአዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎችንና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ጎብኝተዋል። በጎ ፍቃደኛ ወጣት ምርትነሽ ካሳሁን ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ብላለች። በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለገጽታ ግንባታው ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግራለች። በጎ ፍቃደኛ ወጣት ባቻክ ኡጁሉ በበኩሉ በጉብኝቱ የተመለከተው የልማት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስታወቀው። ያገኘሁት ዕድል ለአገሬ የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ ለማበርከት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ብሏል፡፡ ከስልጠናው ባገኘሁት ዕውቀት በመታገዝ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በሚጠበቀው ደረጃ ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ነኝ ሲልም አክሏል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንፍረንስ፣ ሁነትና የመንግሥት ፕሮቶኮል ዳይሬክተር እሸቱ ለገሰ በበኩላቸው፥ በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ እንግዶች ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ እንዲገነዘቡ የሚያስችል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል። በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቁ በጎ ፍቃደኞች ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ዛሬ የተደረገው ጉብኝት ሰልጣኞች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት። የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በረከት ድሪባ በ38ኛው የህብረቱ ጉባኤ የሚሳተፉ እንግዶች የኢትዮጵያን ገጽታ በላቀ ደረጃ እንዲረዱ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። በጎ ፍቃደኞቹ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲን ጨምሮ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ግንዛቤ እንዲጨብጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው ያስታወቁት። ኢትዮጵያ ከኮንፍረንስ ቱሪዝም ይበልጥ እንድትጠቀም የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በርካቶችን ከቄያቸው አፈናቀለ
Dec 1, 2024 2017
አዲስ አበባ፤ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በርካቶችን ከቄያቸው ማፈናቀሉ ተገለጸ። የኬንያ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከባድ ዝናብ እየጣለ ነው። የአደጋ ምላሽ ቡድን አባላት በሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተጎዱ ከ240 በላይ አባወራዎችን አደጋ ከደረሰበት ሥፍራ ማንሳት መጀመራቸውን የሀገር ውስጥና ብሔራዊ አስተዳደር ሚኒስቴር በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁን ዥንዋ ዘግቧል። ሚኒስቴሩ በቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ እና በሰሜን ምዕራብ ክልሎች ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን በመግለጫው አስታውቋል። "የአደጋ ምላሽ ቡድኑ ከብሔራዊ የመንግስት አስተዳደር ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለውን ሁኔታ በመከታተል ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየሰጡ ነው" ሲል ዘገባው አመልክቷል። በሳምንቱ መጨረሻ እርጥበት አዘል አውሎ ነፋሶች ይጠበቃል ሲል ያመለከተው ዘገባው፤ የሰሜን እና ምስራቃዊ ኬንያ እንዲሁም የባህር ዳርቻ እና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የጎርፍ ማስጠንቀቂያዎች መሰጠታቸውንም አክሏል። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ሳምንት ዝናቡ ሊቀንስ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንደሚኖሩ የሚኒስቴሩን መግለጫ ጠቅሶ ዥንዋ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ በተጨማሪም ሀይቅ ዳር በሆነችው ኪሱሙ 200 የሚጠጉ አባዎራዎች መጎዳታቸውን አመልክቶ፤ 100 ሄክታር ማሳ ላይ የተዘሩ ሰብሎች መውደማቸውን ጠቁሟል። "ለደህንነታቸው ሲባል ለጊዜው ወደ ሌላ ቦታ የሚዘዋወሩ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢ ነዋሪዎች የአደጋ ምላሽ ከሚሰጡ ቡድኖች ጋር እንዲተባበሩ ሚኒስቴሩ ማሳሰቡን" ዘገባው አመክቷል። 2024 መጀመሪያ ላይ የጣለው ያልተለመደ ዝናብ ኤልኒኖ ተብሎ ከሚጠራው የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ በሆነችው በኬንያ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ዘገባው አስታውሷል። በኬኒያ በመጋቢት እና ሰኔ መካከል በጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ከ300 በላይ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ያመለከተው ዘገባው፣ በዚህ ወቅት 188 ሰዎች ቆስለዋል፣ 38 የሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ደብዛቸው መጥፈቱን ዘገባው ጠቁሟል። በነዚሁ ጊዚያት በጎርፉ ምክንያት ከ293 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ 306 ሺህ 520 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከብሔራዊ የአደጋ መከላከል ማእከል ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዥንዋ ዘግቧል።
እየተባባሰ የመጣው የሶማሊያ ፖለቲካዊ ቀውስ
Nov 27, 2024 1754
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ በሶማሊያ ፓርላማ ዛሬ ከፍተኛ ብጥብጥ ተከስቷል። የሶማሊያ መንግስት አካሄድን የተቃወሙ የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ቁጣቸውን በፓርላማ ውስጥ ሲገልጹ ታይተዋል። የሶማሊያ ፓርላማ ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ መንግሥት የሶማሊያ ጦር አልሸባብን ከመዋጋት ይልቅ በጎሳ ክፍፍል እንዲወጠር በማድረግ የያዛቸውን ቦታዎች እንኳ እንዳያስተዳድር አድርጓል ብሏል። በሀገሪቱ ሙስና ስር እየሰደደ ከመምጣቱም ባሻገር መንግስት ጦሩን ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመ መሆኑንም ነው ፓርላማው በመግለጫው ያስታወቀው። ይህም በሀገሪቱ የጎሳ ክፍፍል እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል። ከሶማሊያ ህገ መንግስት ባፈነገጠ መልኩ የሀገሪቱ መንግስት የክልላዊ አስተዳደሮችን መብቶች እየተጋፋ መሆኑንም እንዲሁ። የሶማሊያ መንግስት ሶማሊያውያንን በጎሳ ለመከፋፈል የሚያደርገው ሙከራ በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠይቀዋል። የሀገሪቱ መንግስት ከመሰል አደገኛ አካሄዱ ካላቆመም ሶማሊያ የመፍረስ አደጋ እንደሚገጥማት የፓርላማ አባላቱ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
Nov 10, 2024 2405
አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፦ የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በሩሲያ-ሶቺ ከተማ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ተሳትፏል፡፡ ጉባዔው በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያጎላ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በመድረኩ ገልጸዋል። የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን በመድረኩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በአፍሪካ እና ሩሲያ መካከል በተለይም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፎች ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ትብብር ማሳደግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ኢንዱስትሪን ማስፋት የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ቁልፍ መስኮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ ለማድረግ እና አፍሪካ በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንድታገኝ ሩሲያ ድጋፍ ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት ኢትዮጵያ በደስታ ትቀበለዋለችም ነው ያሉት፡፡ ሚኒስትሩ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡
አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ ይገባል
Oct 24, 2024 3386
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 14/2017( ኢዜአ)፦የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከብሯል። በመርኃ-ግብሩ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መልዕክት የድርጅቱ ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ አስተላልፈዋል። ዋና ፀሐፊው በመልዕክታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ከተመሠረተ አንስቶ ላለፉት 79 ዓመታት ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት የላቀ ሚናውን መወጣቱን አስታውሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር፣ የዓለም አቀፍ ሕግ እሴቶችና መርሆዎች በእያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲሁም ሰብአዊ መብቶች ውስጥ ስለመሆኑ አንስተው፤ በቀጣይም ለዓለም ዘላቂ ሰላምና ሰብአዊ መብት መከበር ሁለገብ መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የትምህርት ጉዳዮች አማካሪ ጋኦጋካላ ሌመንያኔ፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል። በተለይም በሰላምና ደህንነት፣ በዘላቂ ልማት እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ እና ሌሎችም ጠንካራ ትብብር መፈጠሩን አንስተዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል ሰሙንጉስ ገብረሕይወት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቷንና አሁንም መቀጠሏን አንስተዋል። ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመቀበል እያስተናገደች ስለመሆኗ አንስተው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧም ይበልጥ ተቀራርባ ለመስራት የሚያግዛት መሆኑን ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ድርጅቱ እ.አ.አ 1971 ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2782 መሠረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ጥቅምት 24 ይከበራል። እለቱ እ.አ.አ 1945 የተቋቋመውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ በማሰብ የሚከበር ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አገራትና ተቋማት የመንግሥታቱን ድርጅት እሴቶች እንዲሁም ዓላማዎች በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እና ተግባራት ይከበራል።
የሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ መጨረሻ
Oct 17, 2024 2513
በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የ70 ዓመቱ የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ለሁለት ወራት የቆየው የክስ ሂደት የሜኔንዴዝን የፖለቲካ ቆይታ እንዲያበቃ ማድረጉን የአሜሪካው የፖለቲካ ዲጂታል ጋዜጣ ፖለቲኮ ዘግቧል። የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግ እና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል ከሰዋል። የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል። የሴናተሩ ባለቤት የሆኑት ናዲኔ ሜኔንዴዝ እ.አ.አ. በማርች 2020 ገደማ ባለቤቷ ሴናተር ሜኔንዴዝ ከአንድ የግብጽ ጦር ጄኔራል ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ማዘጋጀቷንና በፕሮግራሙ ላይም ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር ተገናኝተው በወቅቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ይካሄድ ስለነበረው ድርድር መወያየታቸው የምርመራ መዝገቡ ያመለክታል። ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ዋንኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አድርጋ ስትሰራበት መቆየቷ መዝገቡ ያሳያል። ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር በተገናኙ በቀጣዩ ወር ውስጥ (በኤፕሪል 2020 ወይም ገደማ)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ለሚሳተፉት የአሜሪካ ግምጃ ቤት የቀድሞ ዋና ፀሐፊ ስቴቨን ሙንቺንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውን ይገልጻል። በደብዳቤው ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ያደርጉት የነበረው ድርድር መቋረጥ እንዳሳሰባቸው ለመግለጽ ደብዳቤውን መጻፋቸው ተመላክቷል ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሕዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድግ መጠየቃቸውን በምርመራ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ጠቁሟል። የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል። በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል። ሴናተሩ ጥፋተኛ ከተባሉም በኋላ በሰጡት አስተያየት ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የገባሁትን ቃለ መሐላ አላፈርስኩም ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ውስጥ የሜኔንዴዝ ጠበቆች ለጥፋቶቹ ሁሉ ተጠያቂ ሚስታቸው ናዲን ናት ሲሉ ይወቅሳሉ። የግል ጥቅሞችን ለማግኘት ጥፋቶቹን ፈጽማለች በማለትም ተከራክረዋል። ጥፋተኛ በተባሉባቸው ክሶች ምክንያት ከሰኔቱ እንዲሰናበቱ ግፊት በርትቶባቸው የነበሩት ሜኔንዴዝ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። ሴናተሩ ጥፋተኛ በተባሉባቸው ወንጀሎች የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ለበርካታ ዓመታት በእስር ሊቆዩ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ናቸው። በ2025 ለምን ያህል ጊዜ ይታሰራሉ? የሚለው ጉዳይ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገልጿል። ሜኔንዴዝ እ.አ.አ በ2015 በፌደራል የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የነበረ ቢሆንም ዳኞች የፍርድ ውሳኔ ላይ ባለመድረሳቸው ክሳቸው ውድቅ እንዲሆን መደረጉ የሚታወስ ነው። እ.አ.አ በ2021 ቶም ማሊኖውስኪ፣ በያንግ ኪም፣ ግሪጎሪ ሚክስ ፣ ዴቪድ ሲሲሊን፣ ብራድ ሼርማንና ማይክል ማካውል ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ይታወቃል። ሕጉ በወቅቱ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መርቶት ነበር። በወቅቱ የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው። ሕጉ ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ተወስኖም ነበር። በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበረም ይታወቃል። ሴናተሩ ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱ ከግብጽ ጉቦ ተቀብለው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ጫና እንዲደረግባት ማድረግ ይገኝበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለመጉዳት እየተንቀሳቀሰች ከምትገኘው ግብጽ በቀጣናው ትርምስ ለመፍጠር እየሰራች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈራረሟ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ግብጽ አላስፈላጊ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ለመፍጠር እና የአገርን ስም የማጠልሸት ተግባር እየፈጸመች ትገኛለች። ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እያደረገች ያለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ቀጣናውን ውጥረት ውስጥ የማስገባት እኩይ ዓላማ ያለው ነው። ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻበብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች። ኢትዮጵያ የግብጽን ቀጣናውን የማተራመስ እና ሽብርተኝነትን የመደገፍ አካሄድ የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች። የሶማሊያ መንግሥት ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ መንግስት መግለጹ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በቀጣናው የብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በአንክሮ እየተከታተለች ትገኛለች። ኢትዮጵያን የመጉዳት እና የአባይ ወንዝን እኔ ብቻ በብቸኝነት የመጠቀም አባዜ የተጠናወታት ግብጽ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ እና ከልማት ሕልሟ ልታስቆም አልቻለችም። ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ፍትሐዊነት እና እኩልነት በተሞላባት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የመጠቀም አቋምን በተደጋጋሚ ጊዜ ብታወሳውቅም ግብጽ ይሄን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሉዓላዊ አገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለዜጎች ጠቀሜታ የማዋል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ ተቃርና ቆማለች። ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን የትብብር ማዕቀፎችን መሰረት አድርጋ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ኢ-ሚዛናዊ እሳቤ በውሃ ሀብት የመልማት ጥረቶች እውን እንዳይሆኑ እክል እየፈጠረች ትገኛለች። ግብጽ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ለመቀየር የምታደርጋቸውን ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ሀሳብ ማንጸባረቋን በግልጽ ተቃውማ አቋሟን አሳውቃለች። ግብጽ ጊዜ ያለፈባቸውን የቆዩ ማዕቀፎች ተጠቅማ የናይል ወንዝን እኔ ብቻ ልቆጣጠር የሚለውን ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ ትታ ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራርና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ የድርድር አማራጭን እንድትከትል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል። ግብጽ በቅርቡ ወደ ትግበራ በገባው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በማጽደቅ በቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢና እንድትወጣም ጠይቃለች። ከተፋሰሱ አገራት ጋር ወደ ሰላማዊ የትብብር አማራጭና ውይይት ዳግም እንድትመልስም አሳስበለች። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው በጋራ የመልማት እና በጋራ የማደግ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የጀመረችን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተደማጭነት በማስፋት ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንደምትገፋበትም አመልክተዋል።
ኤጀንሲው ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ነው
Sep 24, 2024 3254
አዲስ አበባ ፤መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ ። የኤጀንሲው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2030 ዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ በማሳደግ የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ የአየር ንብረት ለዉጥ ግቡን ማሳካት እንደሚቻል አመልክቷል። በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በኒውዮርክ የአየር ንብረት ሳምንት ላይ ለታደሙ ከመንግሥት እና ከንግዱ ዘረፍ ለተውጣጡ ኃላፊዎች ሪፖርት ማቅረቡን ዘግቧል። በዱባይ አምና በተካሄደው COP 28 የአየር ንብረት ጉባኤ 200 የሚጠጉ ሀገራት እንደ የንፋስና ፀሀይ ያሉ የታዳሽ ኃይሎችን በሦስት እጥፍ በማሳደግ በ2050 ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን ዘገባው አስታውሷል። አገራት በ2030 ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመተግበር ጥቅም ላይ ለማዋል 25 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመገንባት እና ለማዘመን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አንስቷል። በዚህም በ2030 ዓለም 1 ሺህ 500 ጊጋዋት የኃይል ማከማቻ አቅም እንደሚያስፈልጋት ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል። አገራት በCOP 28 የኃይል አጠቃቀምን የሚረዱትን የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ለማሳደግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ዉጤታማነቱ መንግሥታት ለፖሊሲዎቻቸዉ ቅድሚያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን አመላክቷል። በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት መሰረት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሀገራት ታዳሽና የኢነርጂ ውጤታማነት ግቦችን በአገራዊ ዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት አለባቸው ሲል ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማሳሰቡን ዘገባው ያመለክታል። ከዓለም አቀፉ የኢነርጂ ዘርፍ የተለቀቀው የልቀት መጠን ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ዘገባው አንስቷል። የታዳሽ ኃይል አቅምን በሶስት እጥፍ ማሳደግና የኃይል አጠቃቀምን ለመቀነስ የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ማሳደግ በአሥር ዓመታት መጨረሻ የዓለም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በ10 ቢሊየን ሜትሪክ ቶን ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው ጋር ሲነጻጸር መሆኑን ሪፖርቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።