አካባቢ ጥበቃ - ኢዜአ አማርኛ
አካባቢ ጥበቃ
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Apr 18, 2025 196
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የ2025 ፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ተሳትፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ይህን ጠቃሚ ጉባኤ ላዘጋጀው የቬይትናም መንግስት ምስጋና በማቅረብ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። የ2025 ፒ4ጂ ጉባዔ የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት የአንድነትና የብዝሃነት ሃይል ማሳካት የሚችለውን አቅም አይተናል ብለዋል። የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ይህን ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት እንደሚሰማት ገልጸዋል። ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል። ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና እንዲሁም ወጣቶችንና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ መሳሪያ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሆኗን አመልክተው፤ ይህንን ለመፍታት የተግባር ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2030 እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በተጣጣመ መልኩ እ.አ.አ በ2050 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓት እውን የማድረግ ትልቅ ትልም ማዘጋጀቷን ተናግረዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እና እየተስፋፋ ያለው የታዳሽ ሃይል ልማት ለዚህ ራዕይ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። ይሁን እንጂ የትኛውም ሀገር የአየር ንብረት ቀውስን ብቻውን መቋቋም እንደማይችል አመላክተዋል። ይህንን ችግር የመፍቻ መንገዱ የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የፒ4ጂ በ2018 ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለመድረኩ አስተዋፅዖ ማበርከቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። በምግብ ሥርዓት፣ በታዳሽ ኃይል፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገሩ ከተሞች እና በኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ የትብብር ፕሮጀክቶች አብረን ስንሠራ የሚቻለውን አይተናል ሲሉም ተናግረዋል። እንደ ፒ4ጂ መስራች አባልነቷ፥ ቁልፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ማገገምን እና ዘላቂ ልማትን ለማራመድ ቁርጠኝነቷን እንደምታስቀጥልም ነው ያስረዱት። በዚህ አውድም፥ በቬይትናም መንግስት የቀረበውን የሃኖይ ዲክላሬሽን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል። የቬይትናም መንግስት ይህንን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀቱ፣ ለአረንጓዴና የበለጠ አካታች ዓለም ላበረከቱት አስተዋፅዖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። ቀደምት የሰው ዘርና የቡና መገኛዋን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም ትልቁ የደን ልማት መርሃ ግብር እየተገበረች ያለችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች
Apr 17, 2025 173
አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥የሀኖይ ጉባኤ አነስተኛ ቢሆኑም በሚገባ የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚያስገኙ እና ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ማሳየቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት ይሰማታል ብለዋል። ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን የታየውን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል። ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ብሎም ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ አስፈፃሚ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ ይዘጋጃልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል
Apr 17, 2025 158
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፡-70ኛው አፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም(GHACOF 70) ግንቦት 11 እና 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ፎረሙ የሚካሄደው “የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አቅምን በጋራ ማጠናከር ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፎረሙን እንዳዘጋጀ ተገልጿል። እ.አ.አ ከማርች እስከ ሜይ 2025 ያለው የአየር ንብረት ትንበያ አፈጻጸም ውይይት እንደሚደረግበት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በፎረሙ እ.አ.አ ከጁን እስከ ሴፕቴምበር 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ እንደሚደረግ አመልክቷል። የአየር ንብረት ትንበያ እና አስተዳደር ስትራቴጂዎች ፋይዳ የተመለከተ ውይይትም ይደረጋል። በፎረሙ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮችንና የዘርፉ ተዋንያንን ይሳተፋሉ። ከዋናው ፎረም አስቀድሞ የአየር ንብረት ትንበያ እና ተጓዳኝ አውደ ጥናቶች እንደሚካሄዱ ኢጋድ አስታውቋል። 69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በጥር ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው- አምባሳደር ፍስሃ ሻውል
Apr 16, 2025 257
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ገለጹ። ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከኢስት አፍሪካ የማዕድን ኩባንያ እና ሙገር ሲሚንቶ ኩባንያ የተወጣጣ የከፍተኛ አመራር ልዑካን ቡድን ለጉብኝት ህንድ ኒው ዴልሂ ይገኛል። የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት አላማ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቮች ልምድ ለመለዋወጥ እና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ነው። ልዑኩ በቆይታው በህንድ ያለው የኢንዱስትሪ አሰራሮችን እንደሚጎበኝ በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል። ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል። በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ከልዑኩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከካርቦን ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘቻቸውን ግቦች አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ጉብኝት እ.አ.አ በ2019 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ይፋ የሆነው “Leadership Group for Industry Transition” የተሰኘው የመንግስት እና የግል አጋርነት ኢኒሼቲቭ አካል ነው። ኢኒሼቲቩ በህንድ እና ስዊድን መንግስታት የጋራ ሊቀመንበርነት የሚመራ ሲሆን የኢንዱስትሪ ሽግግራቸው ዘላቂነትን የሚከተል ማዕቀፍ ያላቸው አባል ሀገራት የያዘ ነው። ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በኢኒሼቲቩ አባል የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ውጤት አምጥቷል
Apr 15, 2025 158
አዳማ፤ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ ባለፈ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 15/2017 ዓም ጀምሮ እየተከናወነ ነው። በህዝቡ ንቅናቄ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን ከክልሉ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ነበር ብለዋል። በክልሉ 6 ሺህ 400 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ስራ ለ60 ቀናት በህዝብ ንቅናቄ መከናወኑንም ገልጸዋል። በዚህም በርካታ የክልሉ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ኤሊያስ፤ ''የአካባቢውን ስነ ምህዳር ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረታዊ ስራዎች እየተሰራ ነው'' ብለዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ደርቀው የነበሩ የሀሮማያና ጨርጨርቅ ሐይቅን ጨምሮ ወንዞችና ዥረቶች የተመለሱ ሲሆን አሁን ላይ ለመስኖ ልማት አገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ ብለዋል። እንዲሁም በተፋሰስ ልማቱ በቡና፤ በፍራፍሬ፤ በደን ልማት፤ በሰብል ልማትና በስነ ምህዳር ጥበቃ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ሲሉም ገልጸዋል። ''በተመሳሳይም የአየር ጠባይ ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋምና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር መሸርሸርና መከላት መቀነስ ችለናል'' ብለዋል። በዘርፉ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል አማራጭ መሆኑን የገለፁት ምክትል ሃላፊው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ፤ በእንስሳት መኖ፤ በንብ ማነብና ማር ልማት፤ በእንስሳት እርባታና ማድለብ በባለቤትነት ተረክበው እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል። በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ670 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከንኪኪ ነፃ ተደርጎ እንዲያገግም እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ ተዘጋጅተዋል
Apr 14, 2025 158
አዶላ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ እንዳሉት እስካሁን በዞኑ 13 ወረዳዎች በተካሄደው ስራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል የፍራፍሬ፣ የደን፣ የጥላ ዛፍ፣ የእንስሳት መኖና የቡና ችግኝ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ሃላፊው እንዳሉት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ በዋናነት የቡና፣ አቦጋዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ለደንነት ደግሞ የሀበሻ ጽድ፣ ዋንዛና ኮሶ፣ በብዛት ቀዳሚዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ የውበት የጥላ ዛፍና የእንስሳት መኖ የመሳሰሉት በችግኝ ዝግጅቱ ውስጥ የተካተቱ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተራቆተን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ የችግኝ መትከያ መሬት እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተከላ ስራው በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ184 ሺህ በላይ የሚገመት የዞኑ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡ በዞኑ አዶላ ወረዳ የደራርቱ ቀበሌ ነዋሪና አባገዳ ኦዳ ጎበና አንድ ዛፍ ሲቆረጥ 10 ችግኝ መትከል የተለመደው የገዳ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በአከባቢ መራቆትና በደኖች መመናመን ባለፉት ዓመታት በአከባቢያችን ከተከሰተው ድርቅ ብዙ ነገር ተምረናል ያሉት አባ ገዳው፤ ይኸንን ለመቀልበስ የሚያስችሉ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።፡ ችግኝ ማዘጋጀትና መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያስተማሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጎበና ዱከሌ ችግኝ ተክሎና ተንከባክቦ ማሳደግ ከማንም በላይ የእኛ የወጣቶች ድርሻ ነው ብሏል፡፡ አከባቢን መንከባከብ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባለፉት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ትምህርት መወሰዱን ያስታውሳል፡፡
ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ ተደረገ
Apr 12, 2025 201
አዳማ ፤ ሚያዝያ 4/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆና ሉሜ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ መረሐ ግብር ተካሄደ። ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የግብርና ዘርፍ አመራር አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን የችግኝ ጣቢያዎችና አቮካዶ ክላስተር እንቅስቃሴን በሞጆና ሉሜ አካባቢዎች ተገኝተው ተመልክተዋል። በዘህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ በሞጆ ያየነው የችግኝ ጣቢያ የተደራጀና የተቀናጀ ሳይት ነው ብለዋል። በጣቢያው ከሚከናወነው የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ በተለይ የአቮካዶ ልማት፣ንብ ማነብና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በአንድ ማዕከል እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። በዚህም መልካም ተሞክሮና ልምድ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልላችን ወስደን እንስፋፋለን ሲሉም ገልጸዋል። በአፋር ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የባዮ ዳይቨርሲቲ ዳይሬክተር አቶ አሊ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ ልምድና እውቀት ያገኘንበት ነው ብለዋል ። በተለይ በመስኖ ለምግብነትና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል መረዳታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ ጨዋማና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የመጡት አቶ በየነ በላቸው በበኩላቸው፤ የሞጆ ችግኝ ጣቢያና የአቮካዶ ክላስተር በእውቀትና ክህሎት የተዘጋጀ መሆኑን ከምልከታቸው እንደተረዱ ገልጸዋል። በተለይ አቮካዶ ከማምረት ባለፈ የአቮካዶ ችግኝ ወደ ውጭ ለመላክ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ክልላችን ለአቮካዶ ልማት አመቺ በመሆኑ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ ዝሪያዎች ከኦሮሚያ ክልል ገዝተን የማዳቀል ስራ እየሰራን ነው ብለዋል። የሉሜ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለሚ ይርኮ ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር በፍራፍሬና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም ሞጆን ጨምሮ በወረዳው 150 የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው 35 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ለ4ኛ ጊዜ የአቮካዶ ምርት ከወረዳው በማዕከላዊ ገበያ በኩል ወደ ውጭ መላኩን ጠቁመው፤ በተጨማሪ የተሻሻሉ የአቮኮዶ ችግኞችን ወደ ውጭ ለመላክ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው፤ የመስክ ምልከታው በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በመሬት ላይ ያለውን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደተሰናዳ ገልጸዋል። በተለይ የሞጆ ችግኝ ጣቢያ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞች ዝግጅት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ፋኖሴ ፤ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት 60 በመቶ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖና ለውበት የሚውሉ ሲሆን፤ 40 በመቶ ለደን ልማት ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚገኙትን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖች በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ምክክር ተካሄደ
Apr 12, 2025 130
ደብረብርሀን ፤ሚያዚያ4/ 2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የወፍ ዋሻና የመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖችን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ ምከክር ተካሄደ። የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የአማራ ክልል አካባቢና ደን ባለስልጣን "ዊፎረስት ኢትዮጵያ" ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ አግማስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ጥብቅ ደኖችን በመንከባከብና በማልማት ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው። ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት በማሳደግም ለዘመናት በመጠበቅና በመንከባከብ የኖረውን ማህበረሰብ ከደን ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የጣርማ በርና የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል። ለዚህም የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ለምክክር መቅረቡን አስገንዝበዋል። ይህም በደኖቹ ውስጥ ያሉ እንስሳት፣ እጽዋትና ሌሎች ሃብቶችን ለምርምር በማዋልና የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ደኖቹ የካርቦን ልቀትን በመከላከል ለአለም የሚያበረክቱትን በጎ አስተዋጽኦ በማስጠናት ከካርቦን ሽያጭ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ደን ልማት የሬድ ፕላስ ፕሮግራሞ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማስቻል የስነ ምህዳር ጥበቃው እንዲሻሻል አስችሏል ብለዋል። የዛሬው የውይይት መድረክም ጥብቅ ደኖቹን በማልማትና በመንከባከብ አገራችንን በቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል። ዊ ፎረስት ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር አክሊሉ ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳሉት በተለይም በወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ውስጥ ለጥናትና ምርምር የሚውሉ እድሜ ጠገብ ደኖች ይገኛሉ ብለዋል። ከመንግስት ጋር በመተባበር እምቅ ጸጋ ያለውን ጥብቅ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ 10 ዓመታት ከወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን የካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ በመሆን የአገራችን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል። ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ጥብቅ ደን ሲተዳደር የቆየው የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን በ15 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን 8 ሺህ 739 ሄክታር መሬትን እንደሚሸፍንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል -ግብርና ሚኒስቴር
Apr 12, 2025 120
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እስካሁን በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የሥነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ ልማት ለማልማት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል። ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተፈጥሮን በመጠበቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል። የተፋሰስ ልማቱ የመሬት መሸርሸርን በመከላከል፣የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቋቋም እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል። እንደ አቶ ፋኖሴ ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት በጥቅሉ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሥነ አካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። የሚለማው ቦታም ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ የማድረግ ሥራ ሌላው ከተያዙ ግቦች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 ቀናት እስከ 60 ቀናት የተቀናጀ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ እስካሁንም በበርካታ አካባቢዎች የእርከን፣ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት። በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 20 ሺህ 800 ተፋሰሶችን ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈጻጸም ከእቅድ በላይ በ21 ሺህ ተፋሰሶች መከናወኑን ገልጸዋል። በለሙ ተፋሰሶች ላይ ከ7 ሺህ በላይ ማህበራት በእንስሳት ማድለብ፣የፍራፍሬ ተክሎችን በማልማት እና በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በእርከን እና ውኃ ማቆር ላይ የተጀመሩ ተግባራትን ተጠናክረዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተሰራባቸው አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ነው። በዞኑ የበደኖ ወረዳ አርሶ አደር አህመድ ነጃሺ ከዚህ በፊት ተራቁቶ የነበረው መሬት እሁን እርጥበት መያዝ በመጀመሩ ምርት በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተፋሰስ ልማት ሥራው አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ አካባቢን ተንከባክቦ ለማስረከብ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሳተፉበት መሆኑን ጠቁመዋል። የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደር ኃይሌ ታደሰ በበኩላቸው በተፋሰስ ልማቱ የተለያዩ ፍራፍሬ በማምረት እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል። የተፋሰስ ልማቱ በአካባቢው የነበሩ ምንጮች አገግመው በቂ ውሃ እየሰጡ ነው ብለዋል። ሌላው የወረዳው አርሶ አደር እሸቱ አሰፋ በበኩላቸው፥ በተፋሰስ ስራ ባለሙት መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ነው
Apr 11, 2025 146
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ጉባዔው የሚካሄደው ባለፈው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑም ተጠቁሟል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ከአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ በቀጣይ የአውሮፓውያኑ መስከረም 2025 አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቅሷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ጉባዔው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ገልጸዋል። የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባዔው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ ለማስያዝ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። ስለሆነም ጉባዔው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲም ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ያሳየችውን ቁርጠኝነት እና እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን አድንቀዋል። የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ግብርና ሚኒስቴር
Apr 11, 2025 119
አዳማ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በዘንድሮው የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ እቀባ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑ ተገልጿል። የዘንድሮውን የበጋ ተፋሰስ ልማት ክንውንና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የሁሉም ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤሊያስ(ፕ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የተፋስስ ልማትን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥም ድርቅና ጎርፍን የመቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በተጨማሪም የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራ በዘመቻ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ይዘትና አሰራርን በተከተለ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የባለሙያዎችና የአመራሮች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የዛሬው መድረክ በተፋሰስ ልማቱና በችግኝ ዝግጅቱ ሂደት ላይ ያገጠሙ ክፍተቶች ተገምግመው ችግሮችን በመለየት ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል። ከተፋሰስ ልማት ስራ ጎን ለጎን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም የመትከያ ጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል። የተፋሰስ ልማቱ ከዘመቻ ባለፈ የህዝቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የተደረገና ውጤታማ እየሆነ የመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል። በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ21 ሺህ 379 በላይ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ከ598 ሺህ በላይ ሄክታር ከንክኪ ነፃ የተደረገበት ነውም ብለዋል። በተፋሰስ ልማት ስራው በርካታ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ፋኖሴ አዲስ ከሚሰራው የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በተጓዳኝ አምና የተሰሩትን ዕርከኖች የማደስና የመጠገን ስራ መከናወኑንም አመላክተዋል። ህዝቡ በአማካይ ለሁለት ወራት የተፋሰስ ልማት ስራውን በነቂስ ወጥቶ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።
በክልሉ በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል
Apr 11, 2025 126
ባህር ዳር፤ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ማከናወን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የተካሄደው ከጥር ወር አጋማሽ እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ነው። ለስራውም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎችን በመሳተፍ በ8 ሺህ 400 ተፋሰሶች በተፈጥሮ ሃብት መልማታቸውን ገልጸዋል። ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥም የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች፣ውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦይና የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎችን ከልሎ የመጠበቅ ስራ ይገኙበታል ብለዋል። ህብረተሰቡ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ያበረከተው አስተዋፅኦ በገንዘብ ሲተመንም ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው ጠቅሰዋል። ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የአፈር መከላትን በመቀነስ የሰብል ምርታማነትን መጨመር እንዳስቻለም አስረድተዋል። የክልሉ ህዝብ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ተግባር የሚያስገኘውን ጥቅም በአግባቡ እየተረዳ መምጣቱንም ጠቁመዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር የማታ ቢሰጥ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢያቸውን ወደ ለምነት እንዲመለስ አስችሏል። የመሬታቸው ለምነት በመሻሻሉም ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል። አሁን ላይ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ቀስቃሽ ሳያስፈልገን የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። ቀደም ሲል የተፈጥሮ ሃብት ልማት የተከናወነባቸው ተፋሰሶች በማገገማቸው በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት መልኬ ናቸው። በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር የኔው አላምር በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰራባቸው አካባቢዎች ምንጮች እንዲፈልቁ በማድረጉ በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በዞኑ የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው
Apr 11, 2025 95
ወልዲያ፤ሚያዝያ 3/2017(ኢዜአ )፦በሰሜን ወሎ ዞን ከ563 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የዞኑ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደሳለ ባዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ ነው። በተያዘው በጀት ዓመትም በ563 ሚሊዮን ብር የ22 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በግንባታ ላይ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 1 ሺህ 115 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ደርጅቶችና ከህብረተሰቡ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነቡ የሚገኙት ፕሮጀክቶችም በዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ 3 ሺህ 908 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ የሚገኘው ህብረተሰብም በጉልበቱ፣በቁሳቁስና በገንዘብ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል። አሁን ላይ የሁለቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የ14ቱ አፈጻጸም እስከ 80 በመቶና የቀሪዎቹ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሁሉንም የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በዚህ ዓመት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በሃብሩ ወረዳ የቁጥር 4 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላው አበበ በሰጡት አስተያየት፥ በአካባቢያቸው እየተገነባ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን ተዘጋጅተዋል። በጉባላፍቶ ወረዳ የ018 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማረ መኩሪያው በበኩላቸው ግንባታው እየተጠናቀቀ በሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት ከግማሽ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት መስኖ በማልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማት የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል
Apr 10, 2025 153
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ):-በመዲናዋ የኮሪደር ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች የመከሰት ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አሕመድ መሐመድ ገለጹ፡፡ ኮሚሽነር ኮማንደር አሕመድ መሐመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በመዲናዋ እየለሙ የሚገኙ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማቶች የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር በርካታ ጠቀሜታዎች እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የኮሪደር ልማቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል እና ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት ረገድ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመዲናዋ በርካታ ስፍራዎች ለእሳትና ጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የነበሩ ስፍራዎች የኮሪደር ልማትን ተከትሎ ከዚህ ስጋት ነጻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የቤቶች ማርጀትና ተጠጋግቶ መሰራት፣የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ መደራረብ እና በወንዞች ዳርቻ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባት በቀዳሚነት የሚነሱ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በአዲስ መልክ መሰራታቸውን ተከትሎ በከተማዋ የአደጋ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡ የብስክሌተኛ፣ የሰው እና የመኪና መንገዶች ተለይተው መሰራታቸው የኮሪደር ልማቱ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን መተላለፊያ ሆነው በማገልገል አደጋውን በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ከዚህ በፊት በተለይ የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ተሽከርካሪዎች ውሃ ተመላልሰው ለመቅዳት ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸው እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፥ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በርካታ የውሃ መቅጃ ሐይድራንቶች በአካባቢው መሰራተቻውን ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ረዥም ርቀት መጓዝ ሳይጠበቅባቸው በአቅራቢያ ውሃ ተመላልሰው በመቅዳት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ እንዳስቻለ አስታውቀዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ተደራሽ በሆነበት አካባቢ የሚኖሩት አቶ ጌታቸው ረጋሳ በበኩቸው፥ከዚህ በፊት የቤቶች ግንባታ እጅግ የተጠጋጋና ለአደጋ አጋላጭ ስለነበር ተደጋጋሚ አደጋዎች ይከሰቱ እንደነበር አውስተዋል፡፡ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች አደጋውን ለመቆጣጠር በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ተሽከርካሪዎች ይዘገዩ እንደነበር አስታውሰው፥ የኮሪደር ልማቱ በመሰራቱ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል። መንገዶች ደረጃቸውን ጠብቀው በመሰራታቸው፤ከዚህ ቀደም የሚደርሱ አደጋች መቀነሳቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ስሜነሽ ቤልጅግ ናቸው፡፡ ማሾ አየለ በበኩላቸው፥ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ያደረገ እኛንም ከተለያዩ አደጋዎች የታደገ ነው ብለዋል፡፡
በዞኖቹ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ጽህፈት ቤቶቹ
Apr 9, 2025 139
መቱ/ጊምቢ፤ ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፡- በኢሉአባቦር እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችንና ቅርሶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኖቹ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች አስታወቁ። በምዕራብ ወለጋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ልማትና መድረሻ ቡድን መሪ አቶ ምስጋኑ ደገፋ እንደገለጹት በዞኑ ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ በጥናት የተለዩ 206 የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችና ቅርሶች ይገኛሉ። ከእነዚህ የቱሪስት መስህቦች መካከል ሰው ሰራሽ ሀይቆች የሆነው ጎሚ ግድብ፤ አባ ሴና ተራራ፣ ኢንቶ ግድብ፣ ሎፒ ጥቅጥቅ ደን፣ ሚኒሲ ፏፏቴና ሌሎቹ ይገኙበታል ብሎዋል። ዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩትም እስካሁን ለምቶ የሚፈለገውን ያህል የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ አለመሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ግን በዞኑ የተገኘውን ሰለም በመጠቀም የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎቹን በማስተዋወቅ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት በዞኑ ከሚገኙ 206 የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል በቅርቡ 10 የሚሆኑትን ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። በተመሳሳይ የኢሉባቦር ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ እንደተናገሩት በዞኑ ሰፋፊ የተፈጥሮ ደኖችን ጨምሮ ትላልቅ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች እንዲሁም ታሪካዊና ባሕላዊ ቱሪዚም መስህቦች ይገኛሉ። በዞኑ በተለይ በተፈጥሮ ደን መካከል የሚወርዱ 38 ፏፏቴዎች መኖራቸውን ገልጸው ከነዚህም የሶር ፏፏቴ እንደ ሀገርም በትልቅናቱና መስህብነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። የቱሪስት መስህብ ስፍራዎቹን በአግባቡ በማልማትና በማስተዋወቅ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በዞኑ የሚገኙ የሶር ፏፏቴን ጨምሮ የተፈጥሮና በህላዊ ቱሪዝም መስህቦችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ጥረቱ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል። ዘርፉን በማልማት ሂደት የመንግስትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ለመሸፈን የሚያስችል የችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ ነው
Apr 9, 2025 101
ደሴ፤ሚያዚያ 1/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በደን ለመሸፈን የሚያስችል የችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ መገርሳ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የደን ሽፋንን በማሳደግ፣በተፋሰሶች ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ፣ በመኖ ልማት፣ በንብ ማነብና በፍራፋሬ ልማት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የተገኘውን ጥቅም ለማስፋትም በመጪው ክረምትም ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን ለመሸፈን የሚያስችል ችግኝ ማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል። ችግኞቹ የተዘጋጁት በ24 ሺህ 330 የመንግስት፣ በማህበራትና በግለሰቦች ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መሆኑንም ገልፀዋል። ችግኞቹም አብዛኞቹ የፍራፍሬ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በተለይም አርሶ አደሩና ወጣቶች ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ ከሰብል ልማቱ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ ሀርቡ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሰይድ አህመድ በሰጠው አስተያየት፥ በየዓመቱ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላትና በማዘጋጀት በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮም የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ያመጣውን እድል ለመጠቀም ከ75 ሺህ በላይ የማንጎ፣ አቡካዶ፣ብርቱካንና ሌሎችንም የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግሯል። ሌላው የደሴ ዙሪያ ወረዳ የ025 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉቀን አሊ በበኩላቸው፥ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ዙሪያ የሚተክሉት የባህር ዛፍ፣ አፕልና ጽድ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚተከሉ ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘት ባለፈ ምርታማነታችንን ለማሳደግና የደን መመናመንን ለመከላከል አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት 30 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 80 በመቶው መፅደቅ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች በይፋ ተጀመረ
Apr 8, 2025 129
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚተገበር የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች በይፋ ተጀምሯል። በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌቴ ዘለቀ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ሀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት ለውሃ ሀብት ልማትና ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ዛሬ በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የተፋሰስ ፕሮጀክት የውሃ ሀብትን ከመጠቀምና ከመጠበቅ አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተፋሰሱ አከባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ማሻሻልና ለአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶች የማይበገር አካባቢን በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ ያለመ መሆኑም ተገልጿል። ፕሮጀክቱ በኔዘርላንድስና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር መሆኑም ተመላክቷል።
በድሬዳዋ ለመጪው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው
Apr 8, 2025 108
ድሬዳዋ፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ የደን ልማት እና አየር ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ። በባለስልጣኑ የደን ልማት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ናቸው። በአስተዳደሩ የገጠርና ከተማ ክላስተሮች ችግኝ ጣቢያዎች እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከወዲሁ ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል። በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተከላ እየተዘጋጁ ካሉ ችግኞች መካከል የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንደ ሎሚ፣ ፓፓያ፣ ጊሽጣ፣ ማንጎ፣ ሃምበሾክ፣ ብርቱካን እና የመሳሰሉት ይገኙበታል ብለዋል። እነዚሁ የፍራፍሬና ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለድሬዳዋ አየር ንብረት ተስማሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። ችግኝ ተክሎ ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተተከሉት በርካታ ችግኞች 72 በመቶ መፅደቃቸውንም ተናግረዋል። ይኸም የጎርፍ አደጋን በመከላከል እና የገጠሩን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ ለኢዜአ እንዳሉት ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ እየተዘጋጁ የሚገኙት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው። ችግኞቹ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ለደን፣ ለጥላ እና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉና በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ማስዋቢያነት ጭምር የሚውሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በገጠሩ ክላስተርም ችግኞቹ የሚተከሉበትን ስፍራ የመለየትና ጉድጓዶችን ከወዲሁ የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል። ከማህበረሰቡ ጋርም በመወያየት ከወዲሁ ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በሚመልስ አግባብ እየተከናወኑ ናቸው
Apr 6, 2025 117
ወልዲያ፤መጋቢት 28/2017 (ኢዜአ)፦በሰሜን ወሎ ዞን በወረዳዎችና በከተሞች እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥ አግባብ እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ። በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያን ጨምሮ በወረዳና ንዑስ የወረዳ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራዎች ወደ ተግባር መግባታቸውን የዞኑ ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያው አስታውቋል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ መኮንን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የኮሪደር ልማቱ ከሚካሄድባቸው ከተሞች ሃራ፣መርሳ፣ፍላቂት፣ጋሸናና ኮን ተጠቃሽ ናቸው። የእነዚህን ከተሞች የኮሪደር ልማት ለመገንባት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከህዝብ የተሰበሰበ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን ለኑሮና ለስራ ምቹ ከማድረጉም በላይ ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ አግባብ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ልማቱ ለ350 ስራ አጥ ወገኖች የስራ እድል መፍጠሩን አቶ መኮንን ጠቁመዋል። በሃራ ከተማ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማት ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ያሲን ይማም ናቸው። ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ የተጀመረውን የኮሪደር ልማትን መደገፍ ለስራ እድል ፈጠራና ለኑሩ ምቹ ለማድረግ ትልቅ እቅም እንደሚፈጥር ተስፋቸውን ገልጸዋል። ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ከድር ሱልጣን በበኩሉ፥ በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ እንዳስደሰተው ጠቅሶ፥ ከወጣቶች የሚጠበቀውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው የወልድያ ከተማ ቀድሞ የተጀመረው የኮሪደር ልማቱ በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚታወስ ነው።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረናል - አርሶ አደሮች
Apr 5, 2025 131
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የበደኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። የፍራፍሬ ልማት፣ የንብ ማነብና የእንስሳት መኖ ምርትና ምርታማነት እያደገ መሆኑንም ገልጸዋል። አርሶ አደር ኢብሳ አብደላ፥ አካባቢው ተራራማ በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ እየተሸረሸረ ለረጅም ዓመታት ተራቁቶ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ምርት ለማምረት ይቸገሩ እንደነበር ነው የጠቀሱት። ችግሩን ለመቅረፍም ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የልማት ሥራ በመግባት የአፈር መሸርሸርን የቀነሰ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል። አርሶ አደር አሰን ሸረፍ በበኩላቸው አካባቢው በመልማቱ ምንጮች መጎልበታቸውና ውሃ በቅርበት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአካባቢው መልማት ለእንስሳት በቂ መኖ ማምረት እንዳስቻላቸው አንስተዋል። በዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ የበደኖ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኢብራሂም ዩዬ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተራቁተው የነበሩ ተራሮች በደን እየተሸፈኑ ናቸው ብለዋል። በተፋሰስ ልማት የአካባቢው ነዋሪዎች በማህበር ተደራጅተው በፍራፍሬ ልማትና በንብ ማነብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው፥ ሕዝቡ በሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት የአፈር መከላት እየቀነሰ ለምነት እየጨመረ ነው ብለዋል። የገፀ እና የከርሰ ምድር የውኃ ምንጮች እየጎለበቱ መሆኑንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ባህል እየሆነ መምጣቱን ነው ዋና አስተዳዳሪዋ የገለጹት።