ኢኮኖሚ - ኢዜአ አማርኛ
ኢኮኖሚ
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መስክ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ልማቶች ተከናውነዋል
Apr 22, 2025 24
ሐረር፤ ሚያዝያ 14/2017(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም መስክ የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ። የክልሉ የአስፈፃሚ እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፎች የበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም እየተገመገመ ነው። የግምገማውን መድረክ እየመሩ የሚገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ልማቶች ተከናውነዋል። በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብት እና በመልካም አስተዳደር መስኮች የተከናወኑ ስራዎች የክልሉን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ሃብቶች በላቀ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻሉን በመጥቀስ። እነዚህን ውጤቶች ይበልጥ ለማስቀጠል የግምገማው መድረክ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በግምገማው የተንጠባጠቡ ስራዎችና ክፍተቶች ተለይተው እስከ ሰኔ 30 ድረስ በተቀናጀ መንገድ ለማጠናቀቅ መደላድል ይፈጠራል ብለዋል። በግምግማው መድረክ ላይ የክልሉ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኢብሳ ኢብራሂም የዘጠኝ ወራት የካፒታል ፕሮጀክቶች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በማቅረብ ላይ ናቸው። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ግምገማ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የየወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።
የንብ ማነብ ስራ የአብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ተግባር ነው
Apr 22, 2025 52
አንዳንዶቹ ከመደበኛ ግብርና ጎን ለጎን ያከናውኑታል ሌሎቹ ደግሞ ብቻውን የሙሉ ጊዜ ስራቸው መተዳደሪያቸው ያደርጉታል። በደቡብ ምዕራብ ክልሏ ዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ብቻ በ110 ዘመናዊ እና በ160 ባህላዊ የንብ ቀፎዎች እየተከናወነ ያለው የንብ ማነብ ስራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ። ኤላ ባቾ በተባለችው ቀበሌ ያሉት አርሶ አደሮቹ የማር ምርታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱም ተጠቃሚ አድርጓቸዋል። የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽሕፈት ቤትም በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ሁለንተዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ገልጿል። በጽሕፈት ቤቱ እንስሳትና ዓሳ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ገበየሁ እንደሚያስረዱት ቀደም ሲል ከአንድ ባህላዊ ቀፎ ከ4 እስከ 5 ኪሎ ግራም ማር ይገኝ ነበር። አሁን በስፋት እየተሰራበት ባለው የሽግግር ቀፎም ከ20 እስከ 25 ኪሎ ግራም ማር እየተገኘ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ ከቀፎ አዘገጃጀት ጀምሮ እስከ ማር ቆረጣ ድረስ በዘርፉ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ
Apr 22, 2025 55
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የአህጉሪቷ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ። ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ጉባኤ በስኬት ለማዘጋጀት እያከናወኑ የሚገኙትን ስራ የሚገመግም ስብሰባ አድርገዋል። በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኮሚሽኑ ለጉባኤው እያደረጉት ያለው ስትራቴጂካዊ ዝግጅት ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል። ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለአህጉሪቷ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሄ የሚያበጅ ሆኖ ሁነት እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጉባኤው ትርጉም ያለው ውጤት እና ለውጥ የሚፈጥር ውይይት እንዲካሄድ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። ጉባኤው የአፍሪካ ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የማይበገር አቅም መገንባት እና ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ ስትራቴጂ መቅረጽ የሚያስችል መድረክ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል። ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
አየር መንገዱ እ.አ.አ በ2025 ራዕዩ በአውሮፕላን ቁጥር እና መዳረሻ ብዛት የያዘውን እቅድ አስቀድሞ አሳክቷል - አቶ መስፍን ጣሰው
Apr 22, 2025 56
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ 2025 ራዕዩ በአውሮፕላን ቁጥር እና በመዳረሻ ብዛት የያዘውን እቅድ አስቀድሞ ማሳካቱን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ከጅዌል ኪሪዩንጊ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቆይታቸውም አየር መንገዱ እ.አ.አ በ2025 ራዕዩ በአውሮፕላን ቁጥር እና በመዳረሻ ብዛት የያዘውን እቅድ አስቀድሞ ማሳካቱን ተናግረዋል። አየር መንገዱ እ.አ.አ በ2023/24 ሰባት ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ማግኘቱንና እስከ እ.አ.አ ጁን 2025 ባለው ጊዜ ገቢው 8 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለው ትብብር አውሮፕላን ከመግዛት የገዘፈ መሆኑን ጠቁመው ቦይንግ ለሚያመርታቸው አዳዲስ አውሮፕላኖች የሚሆን የመለዋወጫ እቃዎችን እያቀረበ መሆኑን አንስተዋል። አየር መንገዱ አቅሙን እና ተደራሽነቱን ለማስፋት እያከናወነ ያለውን ስራ አስመልክቶም አቶ መስፍን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም ኩባንያው በአፍሪካ ግዙፍ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመጨረሻ የማስተናገድ አቅሙ ላይ ደርሷል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዓመታዊ የተሳፋሪ የማስተናገድ አቅሙ 25 ሚሊዮን መድረሱን አንስተዋል። አዲስ አየር ማረፊያ መገንባት ያስፈለገውም በአቪዬሽን ዘርፉ በፍጥነት እያደገ ላለው ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መከፈት በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ አስችሏል – የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
Apr 21, 2025 106
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 13/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ዝግ የነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መከፈታቸው በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በበርካታ የለውጥ ሂደት እያለፈች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሰዋል፡፡ ኮሚሽነሩ እንዳሉት፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎች መከፈታቸውን ጠቁመው፥ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ኢንቨስትመንትን ሊደግፉ የሚችሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ህግን በማሻሻል ረገድ የተወሰዱ እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ተገድበው የቆዩ ዘርፎችን የከፈተ መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ የውጭ ኩባንያዎች በጅምላ፣ ችርቻሮ እንዲሁም በወጪ እና ገቢ ንግዶች ላይ እንዲሰማሩ መፍቀዱን ጠቅሰዋል። መንግስት ለረጅም አመታት ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ ሆነው የቆዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ክፍት ማድረጉ ለአብነትም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ኢንቨስትመንቱን የሚደግፉና የውጭ ባለሀብቶች በብዛት መጥተው እንዲሳተፉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ለአብነትም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምናው የ2 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያለው መሳብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ከሪፎርሙ አንጻር ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ከዚህም በላይ መጓዝ እንደሚገባ ጠቁመው፥ የጅምላና ችርቻሮ ወጪና ገቢ ንግድ መከፈቱን ተከትሎ ለ40 የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ 36 የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አጠቃላይ በኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት የማሸጋገር ስልጣን ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ ከጀመረ ወዲህ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሃብቶችን ወደ ቀጣናው እንዲገቡ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በዚህም 11 የሚሆኑ ባለሃብቶች የገቡ ሲሆን አንዳንዶች ሸቀጦችን ጭምር እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል። መንግስት ዝግ የነበሩ የፋይናንስ፣ የቴሌኮምና የንግድ ዘርፎችን ሪፎርም በማድረጉ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመዘገብ እያስቻለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች ነው
Apr 21, 2025 80
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጰያ በግብርና ልማት ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎችን አፈጻጸም በተመለከተ ባለድርሻ አካላት ግምገማ አድርገዋል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አባል ሀገራት የግብርና ልማት አፈጻጸምን በተመለከተ የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም በየሁለት ዓመቱ ይገመግማል። ሀገራቱ ለፕሮግራሙ ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የየሀገራቸውን አፈጻጸም ይገመግማሉ። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያም የግብርና ልማት ስራዎቿን አፈጻጸም ገምግማለች። በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዜና ሃብተወልድ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም የተሻለ አፈፃፀም አላት። ፕሮግራሙ ያስቀመጣቸው መስፈርቶችን በልማት ዕቅዷ በማካተት ተግባራዊ ማድረጓ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ ድርሻ ማበርከቱን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች እያስመዘገበችው ያለው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል። በኢጋድ የምግብ ሥርዓት ፕሮግራም አስተባባሪ ሰናይት ረጋሳ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢጋድ አባል ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስራ ለመስራት እያደረጉ ያለውን ጥረት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል። ፕሮግራሙ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የግብርና ፖሊሲዎች አሰሪ እንዲሆኑ እንዲሁም የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት አያያዝ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ግብርናን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የማገዙ ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። በቀጣናው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ግብርናው በአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያርፍበት መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ዶክተር ሰናይት ገለጻ የቀጣናው ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። ይህንን ችግር ለመቋቋም ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማሳደግ የጀመረቻቸው ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመድረኩ ተነስቷል።
መንግስት የፈጠረው ምቹ ሁኔታ በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ አድርጎናል - ባለሃብቶች
Apr 21, 2025 59
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በማምረቻው እና በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች መንግስት የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ በርካታ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታ በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን በስፋት በማፍሰስ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም መንግስት የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት የዘረጋቸው አዳዲስ የአሰራር ማዕቀፎች በርካቶቹን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ባለሃብቶች መንግስት በልዩ ትኩረት የግሉን ዘርፍ ከማበረታታት ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን ማድረጉ ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ሳቢያ የውሃ ቆጣሪ አምራች ድርጅት ስራ አስኪያጅ አይንሸት አስረስ(ዶ/ር) ከዛሬ ስድስት አመት በፊት የውሃ ቆጣሪ የሚያመርት ድርጅት ማቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ምርታቸውን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለመላክ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለድርጅቱ ስኬት የመንግስት ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ እንደነበር ያነሱት ስራ አስኪያጁ መንግስት ከማበረታታት በተጨማሪ በርካታ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢንዱስትሪ መንደር የማምረቻ ቦታ እንደተሰጣቸው ተናግረው በቀጣይ ምርታቸውን በማሳደግ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡። የማክሮ ፋርም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሲል ታረቀኝ በበኩላቸው የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የተለያዩ የሰብልና የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ መንግስት የውጭ ምንዛሬ እንድናገኝ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ያሉት አቶ ፋሲል አሁን ላይ ምርቶችን ከገበሬዎች፣ ከምርት ገበያ እና ከህብረት ስራ ማህበራት በቀላሉ ለማግኘት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከገበሬዎች ጋር በመተባበር ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንድናመርት ትልቅ እገዛ ተደርጎልናል ነው ያሉት፡። መንግስት ምርቶቻቸውን በቀላሉ ወደተለያዩ መዳረሻ ሀገራት እንዲልኩ የሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጤታማ እንዳደረጋቸው አንስተዋል፡፡ በመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ እና ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሆነም ስራ አስኪያጁ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው በጥራጥሬና ቅባት እህል ዘርፍ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በቀጣይም የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በወልቂጤ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ ነው - አስተዳደሩ
Apr 21, 2025 69
ወልቂጤ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራው እንዲጠናከር ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ንብረታቸውን በማንሳትና ይዞታቸውን በመልቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አስታውቀዋል። የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሙራድ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ በመፋጠን ላይ ይገኛል። የኮሪደር ልማቱም በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደውን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚያሳልጥና የነዋሪውን የልማት ፍላጎት በሚያሳካ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማቱ 25 ኪሎ ሜትር እንደሚያካትት ገልጸው፣ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ህዝብን በማወያየት በማሳተፍና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ልምድ መወሰዱን ገልጸዋል። እንደ ከንቲባው ገለጻ የኮሪደር ልማት ሥራው በከተማው በአራት ሳይቶች ተለይቶ እየተከናወነ ይገኛል። እነዚህም በተለምዶ አደባባይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አንስቶ እስከ ኮሌጅ፣ ከአፓርታማ እስከ ጉብሬ አደባባይ፣ ከጉብሬ አደባባይ ታች ገበያ ወይም መስጊድ እና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እስከ ጉብሬ አደባባይ ድረስ ያካተተ ነው። የኮሪደር ልማት ሥራው የአረንጓዴና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መጋለቢያ እንዲሁም መናፈሻዎችን ባካተተ መልኩ ነው እየተከናወነ መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል። በልማቱ ከተማዋን ከማስዋብና ተወዳዳሪነቷን ከማሳደግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ የህብረተሰቡም የሥራ ባህል እየተቀየረ መምጣቱን ነው የተናገሩት። በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ከአስተዳደሩ እና ከማህበረሰቡ ተሳትፎ መመደቡንም አክለዋል። በኮሪደር ልማት ሥራው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጉልበት ሥራ በማገዝ ልማቱ እንዲፋጠን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ወጣት ቶፊቅ ኢንድሪያስ ተናግሯል። በተለያዩ ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት ሥራ ያስገኘውን ጥቅም በማየቱ ለድጋፍ መናሳቱን ጠቁሞ፣ የከተማው ወጣቶችም ልማትን ከመጠየቅ ባለፈ ለልማቱ ውጤታማነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው መክሯል። ለከተማዋ ልማት የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱልሰመድ አስፋው፣ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ የኮርደር ልማት ሥራዎች ከተማዋ ለረጅም ዓመታት ሳታድግ የቆየችበትን ሁኔታ የሚቀይር መሆኑን አስረድተዋል። በተለይም ከከተማዋ መንገድ መጥበብ ጋር ተያይዞ በዋና መንገድ የሚስተዋለውን የትራፊክ እንቅስቀሴ መጨናነቅ በኮሪደር ልማቱ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የወተትና የሥጋ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ጽህፈት ቤቱ
Apr 21, 2025 54
ደብረ ማርቆስ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተትና የሥጋ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እንስሳትና አሳ ሃብት ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ቡድን መሪ አቶ ጤናው ወንድም አማሽ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ አርሶ አደሩን ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በእንስሳት ሃብት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ። በበጀት ዓመቱ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከ54ሺህ በሚበልጡ ላሞች ላይ የዝርያ ማሻሻል ሥራ ለመስራት ታቅዶ በ9ኝ ወሩ ከ19ሺህ በላይ ላሞች ላይ የማዳቀል ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። በኮርማ በማስጠቃትና በዘመናዊ የማዳቀያ መንገዶች ከተዳቀሉ ላሞችም ዝርያቸው የተሻሻሉ ከ9ሺህ 400 በላይ ጥጆች መወለዳቸውን አብራርተዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከአምስት ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል። ዝርያቸው የተሻሻሉ ለሞችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የሌማት መርሀ ግብርን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆን ያስታወቁት ቡድን መሪው፣ የዝርያ ማሻሻል ሥራው የአካባቢው ላሞች በቀን ይሰጡት የነበረን ከሁለት ሊትር በታች የወተት ምርት በቀን ከ10 ሊትር በላይ ወተት ለማምረት ማስቻሉን ገልጸዋል። በሥጋ ምርትም ዝርያቸው ከተሻሻሉ ከብቶች በአማካይ እስከ 30 ኪሎ ግራም ጭማሬ እንዳለው ጠቁመው፣ ይህም የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አስገንዝበዋል። በአነደድ ወረዳ የአምበር ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሉሰው ማስረሻ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት ከተዳቀሉ ሁለት ላሞች በቀን እስከ 18 ሊትር የወተት ምርት በማግኘት ከሽያጩ ገቢያቸውን እያሳደገ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ከወተት ልማት ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግም ሁለት ላሞቻቸውን በተሻሻሉ ኮርማዎች ማዳቀላቸውን ጠቁመዋል። በእዚሁ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደርብ ካሳ በበኩላቸው ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞችን በማርባት ከወተት ሽያጭ በተጨማሪ ጥጆችን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከዞኑ እንስሳትና አሣ ሃብት ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳያው በዞኑ ቁጥራቸው እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት ይገኛሉ።
በክልሉ ለመኸር እርሻ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው
Apr 21, 2025 49
መቀሌ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ለመኸር እርሻ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን የኩታ ገጠም አስተራረስ እና የእርሻ ሜካናይዜሽንን የማጎልበት ተግባር ትኩረት እንደተሰጠው ተገልጿል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው፤ በተያዘው የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን የምርጥ ዘር እና ሌሎች የግብአት አቅርቦት ሟሟላት የሚያስችሉ ተግባራት ቀደም ብለው መጀመራቸውን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ባለፈው የምርት ዘመን በአርሶ አደሩ እና በምርምር ተቋማት ከተባዙት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ምርጥ ዘር የመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን እና ከህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ጋር በመተባበር ለምርት ዘመኑ የሚሆን ከ100ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ አሁን በስርጭት ላይ ይገኛል ብለዋል። በክልሉ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በኩታ ገጠም/ክላስተር/ እርሻ የስንዴ፣ የማሽላ፣ የጤፍና የሰሊጥ እና ሌሎች ምርቶችን ለማልማት 250ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። ከ130ሺህ ሄክታር የሚበልጠውን መሬትም በትራክተሮች በሜካናይዜሽን ማልማት የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ተክላይ አበበ(ዶ/ር)፤ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳለጥ በ947 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በመጪው ክረምት ከ800 በላይ ኩንታል የመስራችና ቅድመ መስራች ምርጥ ዘር ለማከፋፈል መታቀዱን ገልፀዋል። በአክሱም ከተማ የሚገኘው የምዕባለ የምርጥ ዘር ማባዛትና ግብይት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ግሩም ገብረሰላማ በበኩላቸው ዩኒየኑ ግብርናን ለማዘመንና ምርትን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። ዩኒየኑ ከምርምር ማዕከላት የሚወጣን ምርጥ ዘር የማባዛትና የማከፋፈል ስራ በማከናወን የግብርና ግብዓቶችን ለሟሟላት ጥረት እያደረገ መሆኑና ለመኸር ወቅትም 7ሺህ 400 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማከፋፈል ማቀዱን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸውና ተወዳዳሪነታቸው እያደገ መጥቷል - ሚኒስትር መላኩ አለበል
Apr 21, 2025 50
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ የሚመረቱ ምርቶች ከአመት አመት አይነታቸው ጥራታቸው እና ተወዳዳሪነታቸው እያደገ መምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ንቅናቄው በኢትየጵያ የተለያዩ ምርቶች እንዲመረቱ ከማስቻሉም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በማስቀረት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ሚኒስትር መላኩ አለበል ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትየጵያ ታምርት ንቅናቄ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ባለፉት አመታት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ እንዲሁም ትስስር አንዲፈጠርላቸው በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት የሚመረቱ ምርቶች ከአመት አመት አይነታቸው ጥራታቸውና ተወዳዳሪነታቸው እያደገ መምጣቱንም አስታውቀዋል፡፡ መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ የሚስተዋለውን የቅንጅት ችግር መቀረፉንም አስረድተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም አምራቾች ውጤታማ የማምረት ስራ ውስጥ መግባት መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ የማኑፋክቸሪንግ ካውንስል መቋቋሙና ወደ ስራ መግባቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ቬይትናም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምትከተለው የተሰናሰለ የሰው ሃብት ልማት ትምህርት የሚወሰድበት ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
Apr 21, 2025 46
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ቬይትናም ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የምትከተለው የተሰናሰለ የሰው ሃብት ልማት ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑክ በቬይትናም ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል። የልዑኩ አባል የነበሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የቬይትናም ይፋዊ የስራ ጉብኝትን አስምልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም የቬይትናም የስራ ጉብኝት የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ ከሌላው ዓለም ጋር በማገናዘብ ያልታዩና ትምህርት የሚወሰድባቸውን ተሞክሮዎች ለመቅሰም ዕድል የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ቬይትናም እንደኢትዮጵያ ሁሉ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በማለፍ በብዝኅ የኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ ቅኝት ዕድገትን በማስቀጠል ምቹ ዕድል የፈጠረች ሀገር መሆኗን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ለብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ትኩረት መሰጠቱ ሁለንተናዊ የዕድገትና ብልጽግና ዕድሎችን ፈጥኖ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል። ቬይትናም ከግብርና መር ኢኮኖሚ በመላቀቅ ስኬት እያስመዘገበች የምትገኝበት የከተማና ገጠር ልማት ተግባርም በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የእኛ አቅጣጫ ነባራዊ ሁኔታን በመጠቀም ዕድገትን የሚያመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ በቬይትናም ቆይታም የተያዘው አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ መሆኑ ግንዛቤ የተወሰደበት ነው ብለዋል። ቬይትናም በሰው ሃብት ልማት የትምህርትና ስልጠና ያደረገችው ቁልፍ ሽግግርም ለተከተለችው የልማት አቅጣጫ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ የተቃኘ ሥርዓት መሆኑን አንስተዋል። የቬይትናም መደበኛና ኢ-መደበኛ የትምህርትና ስልጠና የሰው ሃብት ልማት በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሰጠው ተልዕኮ ልምድ የሚወሰድበት ነው ብለዋል። በዚህ መነሻነትም በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮ-ቬይትናም መካከል የሰው ሃብት ልማት ምርታማነትን የሚያሳድግ የትምህርትና ስልጠና የትብብር መግባቢያ ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል። በኢትዮጵያም በአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ፈጠራን የሚያበረታታ ገበያ መር የሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም በራሷ እሳቤና አቅጣጫ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ስኬት እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር መሆኗን አብራርተዋል። በቬይትናም ጉብኝትም የእርስ በእርስ ልምድና ተሞክሮን በመጋራት የሀገራቱን ዕድገት ለማስቀጠል ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን አስረድተዋል።
የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለማቃለል እየሰራ ነው - ከተማ አስተዳደሩ
Apr 21, 2025 61
አዳማ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና እና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በውስጡ በማደራጀት በከተማዋ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት የማቃለል ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ። የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ እንዳሉት አስተዳደሩ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ የከተማ ግብርና ኢንሼቲቮችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። በዚህም የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና እና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በውስጡ በማደራጀት በከተማዋ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት የማቃለል ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል። የኢንቨስትመንት ግሩፑ በማህበር ተደራጅተው በወተት ልማት እና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ምርቶቻቸውን በስፋት ለገበያ እንዲያቀርቡ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የበዓል ገበያም የተረጋጋ እንዲሆን ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የግብይት ቦታን በማዘጋጀት ጭምር በኢንቨስትመንት ግሩፑ ውስጥ የተደራጁ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማድረስ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል። አስተዳድሩ ከ2ሺህ 900 በላይ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታና የእንቅላል ምርት ማዕከላት እንዲሁም የምግብ ዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪን በራሱ በማቋቋም የዋጋ ንረት ተፅዕኖን በዘላቂነት የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። ለበዓላቱም ከሳምንታት በፊት ዝግጅት በማድረግ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ወደ ግብይት ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። በተለይም ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል መስተዳድሩ የእንስሳትና ተዋፅኦ ምርቶችን ማለትም 10ሺህ ዶሮና ከ100ሺህ በላይ የእንቁላል ምርት፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረጉን ገልፀዋል። የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመግታት በወተት ላሞች ልማት፣ በዶሮ እርባታና በእንቁላል ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳትና ዶሮ መኖ ማቀነባበር ስራ ላይ በመሰማራት ከውጭ የሚገባውን መኖ መተካት የሚያስችል ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
አየር መንገዱ ወደ ናይጄሪያ ኢኑጉ ከተማ የሚያደርገውን በረራ በጊዜያዊነት አቋረጠ
Apr 21, 2025 81
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጄሪያዋ ኢኑጉ አካኑ ኢብያም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያደርገውን በረራ እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ማቋረጡን አስታወቋል። በረራው የተቋረጠው በአውሮፕላን ማረፊያው እየተከናወነ በሚገኘው የጥገና ሥራ ምክንያት መሆኑንም አየር መንገዱ ገልጿል። በበረራው መቋረጥ ምክንያት ደንበኞቹ ላይ ለሚደርሰው መጉላላት ይቅርታ የጠየቀው አየር መንገዱ፣ ውሳኔው የደንበኞቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተደረገ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ደንበኞች ለሚኖራቸው ማንኛውም ጥያቄ የሚከተሉትን አድራሻዎች መጠቀም እንደሚችሉም ገልጿል። Ethiopian Airlines Global Customer Interaction Center at +251 116 179 900 Ethiopian Airlines Enugu Office at +2347033745716, +2349033265850
ኮሌጁ የግብርና ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ይፋ አደረገ
Apr 20, 2025 122
ጅማ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ)፦የጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የግብርና ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ይፋ አደረገ። የጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መሀመድ አብደላ፤ ኮሌጁ በተለይም የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዙ ፈጠራዎች ላይ በማተኮር እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች በማንዋል የሚሰሩባቸው ቀላል ማሽነሪዎች መፍጠር መቻሉን አንስተዋል። የበቆሎ መፈልፈያ፣ እና የሩዝ መውቂያ፣ የመኖ መፍጫና ሌሎችም ቀላል ማሽነሪዎች ከኮሌጁ ፈጠራዎች መካከል መሆናቸውን ዲኑ ጠቅሰዋል። እነዚህ ማሽኖች በፍጥነት ስራዎች እንዲጠናቀቁ በማድረግ የአርሶ አደሮችን ጊዜና ጉልበት ከመቆጠብም ባለፈ የምርት ብክነትን የሚያስቀሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በብዛት ከተመረቱ በኋላ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ እቅድ መኖሩን ጠቁመው፥ የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዙ ፈጠራዎች ላይ በማተኮር የፈጠራ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። ከኮሌጁ መምህራን መካከል ዋሲሁን ደሳለኝ የፈጠራ ውጤቶቹ በተለይም ለአርሶ አደሩ አጋዥ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ለአገልገሎት እንዲበቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በቀጣይም የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዙ ቀላል ማሽነሪዎችን በመፍጠር የግብርና ስራዎችን ለማቅለል የሚያስችሉ ፈጠራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ የበዓል ገበያ አስፈላጊ ምርቶች በበቂ መጠን ቀርበዋል - ሸማቾችና ነጋዴዎች
Apr 19, 2025 128
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የበዓል ገበያ አስፈላጊ ምርቶች በበቂ መጠን መቅረባቸውን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለፁ። በነገው እለት የትንሳኤ በዓል የሚከበር ሲሆን ኢዜአ የበዓሉ ግብይት ድባብ ምን ይመስላል የሚለውን ተዘዋውሮ ቃኝቷል። ተዘዋውረን ባየናቸው የሸጎሌ የእንስሳት እንዲሁም የፒያሳ የእሁድ ገበያዎች ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ቀርበዋል። በሸጎሌ የከብት ገበያ ያነጋገርናቸው አንዳርጌ ታደሰ እንዳሉት፤ ለበዓሉ በቂ የሆነ የእንስሳት አቅርቦት አለ። ሌላው አስተያየት ሰጪ ንቁ ፈርጃ በበኩላቸው፤ በገበያው በቂ የእንስሳት አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል። ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ብርሃኑ ጮንቄም እንዲሁ በአቅም ልክ ግብይት መፈፀም የሚቻልበት ገበያ መኖሩን ተናግረዋል። በገበያው የእርድ እንስሳት ሲሸጡ ያገኘናቸው ዚያድ አሊይ በበኩላቸው፤ ለበዓሉ በቂ የእርድ እንስሳት ይዘው መቅረባቸውንና ሸማቾች እየተገበያዩ መሆናቸውን ገልፀዋል። ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ሁሴን ሳኒዮአሊ በበኩላቸው፤ ለበዓሉ በቂ አቅርቦት በመኖሩ ሸማቹ በአቅሙ እየተገበያየ ይገኛል ብለዋል። በፒያሳ የእሁድ ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ሸማቾች በበኩላቸው፤ በእሁድ ገበያ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የዓይኔአበባ ጌታቸው በእሁድ ገበያ የህብረተሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ ምርቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ሲዳ ከበደ እንደገለጹት፤ አቅምን ያገናዘበ አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል። በእሁድ ገበያ ምርታቸውን ይዘው ከቀረቡት ነጋዴዎች መካከል እምሻው ብርቄና ሄለን ብስራት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን መረዳዳት ባህላችን ነውና በዓሉን ያለው ለሌለው በመስጠት ሊያሳልፍ እንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።
በመዲናዋ ለበዓል የሚሆኑ የእርድ እንስሳት በበቂ መጠን ቀርበዋል - ሸማቾች
Apr 19, 2025 102
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ለትንሳኤ በዓል የሚሆኑ የእርድ እንስሳት በበቂ መጠን መቅረባቸውን ኢዜአ ሲገበያዩ ያገኛቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ። ኢዜአ የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የእርድ እንስሳት የግብይት ሁኔታን ተዘዋውሮ ተመልክቷል። በዚህም የቁም እንስሳት ግብይት አቅርቦት በተሻለ ሁኔታ መኖሩንና መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ሸማቾች ተናግረዋል። በሾላ ገበያ ዶሮ እና እንቁላል ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ፤ ለበዓሉ በቂ የእንስሳት አቅርቦት እንዳለ አስተያየታቸው ሰጥተዋል። በቂ አቅርቦት መኖሩ ሁሉም ባለው አቅም መርጦ በመግዛት በዓሉን እንዲያከብር ያስችለዋል ሲሉ ነው የጠቀሱት። በአዲሱ ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ይታገሱ በቀለ እና ስዩም ተፈራ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ቢኖረውም ገበያው ላይ በቂ አቅርቦት በመኖሩ እንደአቅማቸው መግዛታቸውን ገልጸዋል። የበግና ፍየል ገበያ ከሌሎቹ የበዓል ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ ቢያሳይም ከአርሶ አደሮቹ በጥሩ ዋጋ መግዛት መቻላቸውን አቶ ዘሪሁን ወልዴ የተባሉ ሸማች ተናግረዋል። አቶ ምሳዬ ተፈራ፣ አቶ አንዷለም እሸቴ እና አቶ ዘለቀ እጅጋየሁ በሰንጋ ገበያው በቂ አቅርቦት መኖሩን ነው የተናገሩት። አስተያየት ሰጪዎቹ በአሉን ስናከብር ጧሪ የሌላቸውንና አቅመ ደካማ ወገኖችን በመጠየቅና ካለን በማካፈል ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የበዓሉ አስተምህሮም ይህንኑ የሚያጎለብት መሆኑን አመልክተው፤ የበዓሉን እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በቬይትናም በሩዝ ምርት እና የእሴት ሰንሰለት ላይ በጋራ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተደርገዋል - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)
Apr 19, 2025 114
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ በቬይትናም ቆይታ በሩዝ ምርት እና የእሴት ሰንሰለት ላይ በጋራ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ቆይታን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ቬይትናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጣይነት ያለው እድገት በማስመዝገብ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገራት የገባች መሆኗን አንስተዋል። በተለይም የግብርና ልማቷን በማዘመን ትልቅ እድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል። ባለፉት 20 እና 30 አመታት በግብርና ላይ በሰራችው ስራ አሁን ላይ በአለማችን ከፍተኛ የቡና አምራች እና ላኪ ሀገር መሆን መቻሏንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያም አንዷ ከፍተኛ የቡና አምራች ሀገር መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ቬይትናም በሩዝ እና በአትክልት እንዲሁም ፍራፍሬ ትልቅ አቅም መፍጠሯን አንስተዋል። ቡና ኤክስፖርት በማድረግ 4 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ጠቅሰው፤ ከዚህም ብዙ ልምድ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻርም በተለይ በሩዝ ላይ ትልቅ ስራ መስራቷን ለመመልከት መቻሉን ገልጸዋል። በ7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ በማልማት 24 ሚሊዮን ቶን ምርት እንደምታገኝ ተናግረዋል። ኢትዮጵያም ባለፉት ሁለት አመታት ወደ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ማምረት መጀመሯን በመግለጽ። በቬይትናም ቆይታም በስንዴ የተሰራውን ስራ በሩዝ ላይ መድገም የሚያስችል የተሞክሮ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል። በሩዝ ምርት እና የእሴት ሰንሰለት ላይ በጋራ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። ከአትክልት እና ፍራፍሬ ስራዎች አንጻር የሚወሰደው ተሞክሮ ምርቶቹ ሳይበላሹ የሚጓጓዙበት ስርዓት መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ምርቶቹን ከመነሻቸው ጀምሮ የሚሰበሰቡበት መንገድም ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን እና ይህም የድህረ ምርት ብክነት የቀነሱበትን መንገድ እንደሚያሳይም ተናግረዋል። በታዳሽ ሀይል፣ በስማርት ሲቲ ግንባታ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር የተላመደ የአኗኗር ዘዴያቸው አስደናቂ መሆኑን በመጥቀስ። ቀጣይነት ያላቸውን ስራዎች ማከናወን ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አደገ ኢኮኖሚ መሻገር እንደሚቻል ቬይትናም ማሳያ መሆኗንም ተናግረዋል።
ከአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መስፈንጠር እንደሚቻል ከቬይትናም ተሞክሮ መቅሰም ተችሏል
Apr 19, 2025 87
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ ከአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መስፈንጠር እንደሚቻል ከቬይትናም ተሞክሮ መቅሰም መቻሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ገለጹ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ(ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ቆይታን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ቬይትናም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታን ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል፡፡ በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አማራጭ የኢንቨስትመንት ማዕከል በመሆን ትልቅ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቁመው፤ በዚህም የአምራች ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ከቬይትናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢንዱስትራላይዜሽንን ለማስፋት የሄዱበት መንገድ በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚኖር ጂኦፖለቲካዊ አካሄዶችን በማየት የወሰዱት እርምጃ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳቡንና ይህም ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን አንስተዋል። ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችንና አዝማሚያዎችን በመተንተን ኢንዱስትሪዎች ወደ ሀገር እንዲመጡ መሳብ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ቬይትናምን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የስበት ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል። እንዲሁም ከትንንሽ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መስፈንጠር እንደሚቻልም ከቬትናም ተሞክሮ መቅሰም መቻሉን ገልጸዋል። ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ግብዓት እንዲጠቀሙ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ነው ዶክተር ፍሰሃ ያብራሩት።
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ይዘው እየሰሩ ነው
Apr 19, 2025 65
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ይዘው እየሰሩ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ቆይታን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ቬይትናም ከ20 እና 30 ዓመት በፊት በጦርነት የተጎዳች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፏን አንስተዋል። ኢትዮጵያ የልማት ትልሟን ለማሳካት የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አውጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፣ ቬይትናምም በተመሳሳይ የልማት ዕቅዷን ለማሳካት ባደረገችው ትጋት ውጤታማ ሆናለች ብለዋል። ሀገሪቱ በኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ባሳየችው እመርታ የዓለም የምርት ማዕከል መሆን መቻሏንም ነው ያነሱት፡፡ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዕቅድን በአግባቡ ለመፈጸም መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነትና የህዝብ ድጋፍ መሆኑን ነው ያነሱት። ኢትዮጵያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለችው ጥረት ውጤታማ እንደሚሆን ከቬይትናም ልምድ የወሰደችበት ነው ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ተመሳሳይ ራዕይ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ ንጹህ፣ አረንጓዴ፣ ለኑሮ አመቺና ዘላቂ ከተማ ለመገንባት እያደረገች ያለችው ጥረት ከቬይትናም ጋር እንደሚያመሳስላትም ገልጸዋል። በጉብኝቱ ስማርት ሲቲ ግንባታ ላይ ቬይትናም ያላትን ልምድ መቅሰም መቻሉንም ነው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ያብራሩት።