ፖለቲካ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክርና ተሞክሮ የተቀሰመበት ነው
Apr 21, 2025 114
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቬይትናም ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክርና ተሞክሮ የተቀሰመበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በቬይትናም ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም ቆይታቸው ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡ የቬይትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግስታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ደማቅ አቀባበል በማድረግ መወያየታቸውንም አንስተዋል፡፡ በውይይታቸውም በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል፡፡ ቬይትናም በብዛት የምትታወቀው መዋዕለ ንዋይ በመሳብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ተሞክሮ መቀሰሙን ገልጸዋል፡፡ ከሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ በኢነርጂው ዘርፍ መዋእለ ነዋይ በማፍሰስ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታት እንደሚገባ ማንሳታቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት በቀዳሚነት የምታደርገው ጥረትና በአህጉሪቱ ይኸው መንጸባረቅ እንዳለበት መግለጻቸውን ሀላፊዋ አንስተዋል። ሀገር በቀል የሆኑ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን መግታት የሚያስችሉ ኢንሼቲቮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ መጥቀሳቸውን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ግስጋሴ በጉብኝቱ ከቬይትናም ሰፊ ልምድ የቀሰመችበት፣ በግብርና በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎችም በርካታ ተሞክሮ የወሰደችበት እንደነበረም ገልጸዋል። በተጨማሪም የቬይትናም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል የሁለትዮች ምክክር የተደረገበት ነውም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቬይትናም ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የትብብር አድማስ ያሰፋ ነው - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)
Apr 21, 2025 92
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የትብብር አድማስ ያሰፋ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለፁ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ይፋዊ ጉብኝትን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) እንዳሉት ቬይትናም በሩዝ፣ በቡናና በሌሎች የግብርና ምርቶች ራሷን ከመቻል አልፋ ከፍተኛ ምርት ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ከስንዴ ቀጥሎ ለሩዝ ምርት ትኩረት መስጠቷ መገለፁን አውስተዋል። ቬይትናም የሩዝ ምርትን ለማስፋፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና ምርት እና በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ልምድ ማግኘት የሚቻልባት ናት ብለዋል። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ከቬይትናም ጋር ተመሳሳይና ልምድ የሚገኝበት እንደሆነም ነው ያስረዱት። ቬይትናም ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኤክስፖርት መር ኢኮኖሚ መገንባቷን ጠቅሰው፥ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷ ጠቅሟታል ብለዋል። በአምራች ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዘ ኢንዱስትሪ መገንባቷን በማውሳት፥ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ ምርት በስፋት እያመረተች ወደ ውጭ እንደምትልክም አስረድተዋል። ኢትዮጵያም ተኪ ምርቶችን ለማምረት በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በጨርቃጨርቅና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ እየሰራች በመሆኗ ከቬይትናም ልምድ መቅሰም የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል። በሃዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የቬይትናም ባለሃብቶች ገብተው እየሰሩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የሀገሪቱ ባለሀብቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው በከተማ ግንባታ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን መጎብኘታቸውንና በዚህም የኮሪደር ልማትን ይበልጥ ማጎልበት የሚያስችሉ ልምዶች የተቀሰሙበት ነው ብለዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በጋራ ልማት በተለይም በድህነት ቅነሳ ላይ ከቬይትናም ጋር መስራት የሚያስችሉ ውይይቶች በማድረግ መግባባት መፈጠሩን ጠቁመዋል። የቬይትናም መሪዎች ኢትዮጵያ ቬይትናምን ከአፍሪካ ጋር የምታስተሳስር ስትራቴጂካዊ አጋር አድርገው እንደሚወስዷት መግለጻቸውንም አንስተዋል። ኢትዮጵያም በእስያ ለምታደርጋቸው ግንኙነቶች ቬይትናምን ስትራቴጂካዊ አጋር አድርጋ መውሰድ እንደምትችል መገንዘብ መቻሉንም ነው ያብራሩት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ሀኖይ ቀጥታ በረራ ለመጀመር ስምምነት ማድረጉ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ከቬይትናም ጋር ለማገናኘት ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል። የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንደሚያጠናክርም ጨምረው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ልዑክ በቬይትናም ባደረገው ውይይት ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ሌሎች ዘርፎችም የትብብር አድማሳቸውን ለማስፋት መስማማታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው- ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)
Apr 18, 2025 277
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከአሁናዊ የብልፅግና እይታና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ ሲሉም ገልጸዋል። የሚኒስትሩ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ቆይታ‼ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በቬየትናም የነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት የተሳካና ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ አገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ከአሁናዊ የብልፅግና እይታና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ አገር እየሆነች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በያዝነው ሳምንት ለይፋዊ መንግስታዊ ጉብኝት ወደ ቬትናም አቅንተው ነበር። ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1976 ወዲህ በሀገር መሪ ደረጃ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ላለፉት 50 ዓመት ያህል በመሪዎች ደረጃ ያልነበረውን ግንኙነት የቀየረ እጥፋት ሆኗል። በዚህም ምክንያት ቬየትናም በመሪዋ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን የቆየ ወዳጅነትና ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክር፣ የመሪያችንንና የህዝባቸውን ክብር የሚመጥን እጅግ የደመቀ አቀባበል አድርጋላቸዋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ከሆነው የቬየትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ የሰከነ እና ጥልቀት ያላቸው ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እና ልዑካቸው፣ ከሀገሪቱ ቁልፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋርም የመወያየት እድል አግኝቷል፡፡ የሮቦቲክ እና ሃይቴክ ኢንዱስትሪዎችንም ጎብኝቷል፡፡ ኦሽን ፓርክ በመባል የሚታወቀውን በሀገር በቀል ኩባንያ የሚለማ የከተማ ግንባታ ስራዎችንም ተመልክቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸዉ በሁለትዮሽ እና ብዝሃ ግንኙነቶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ከማድረጋቸውም በላይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሰው ሀብት ልማት እና አቪዬሽን ኢንደስትሪ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነቶች ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ልዑኩ፣ አጋርነት ለዕድገት እና ልማት (P4G) ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ልምድና ተሞክሮ አካፍሏል፡፡ የደቡብ ምስራቅ እስያ አካል የሆነችው ቬየትናም ከቀጠናው አገሮች እጅግ በመዘግየት ማለትም በ1986 በሯን ለዓለም የከፈተችና የኢኮኖሚ ሪፎርሟን የጀመረች አገር ናት፡፡ ለሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ፈጣን እድገት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢኮኖሚ ሪፎርሟ ዶይ ሞይ (Đổi Mới) ወይም Economic renovation through opening up በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ ቬየትናም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በጠንካራ ፓርቲ የሚመራ ጠንካራ መንግስት በመገንባቷ ባለፉት 30 ዓመታት እጅግ አስደናቂ የሚባል የኢኮኖሚ እድገትና ማህበራዊ ለውጥ ያስመዘገበች ሀገር ናት፡፡ ከ1990ዎቹ በፊት እጅግ ደሃ ከሚባሉ ሀገሮች ታርታ ተሰላፊ የነበረች ሲሆን፣ ከነበረችበት እጅግ ጥልቅ የሆነ ድህነት ተነስታ በአንድ ትውልድ ብቻ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ የቻለች ሀገር ናት፡፡ ቬየትናም ዛሬ በምግብ ሰብል ራሷን ከመቻል አልፋ በቀጠናው በግብርና ምርቶች በተለይም በሩዝ፣ በቡና፣ ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶች ግምባር ቀደም ላኪ ሀገር መሆን ችላለች፡፡ የከፍተኛ አምራች ኢንደስትሪ ማዕከል (Industry Hub) በመፍጠር በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ የኤሌክትሮኒክስ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የመጫሚያ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ኤክስፖርት ከሚያደርጉ አገሮች ተርታ የምትሰለፍ ናት፡፡ በጠንካራ ፓርቲ የሚመራው የቬየትናም ጠንካራ መንግስታዊ ቢሮክራሲ፣ ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ በተለይም ለግብርና ልማት እና ኤክስፖርት መር አምራች ኢንዱስትሪዋ ስኬታማነት የላቀ አበርክቶ አለው፤ ሀገሪቱ በዚህ እይታ በአለም አቀፍ ደረጃና በቀጠናው ለነጻ የንግድ ስምምነቶች እና ዝቅተኛ ታሪፍ እንዲሁም በክህሎትና እውቀቱ የበለፀገ የሰው ኃይል ልማት የሰጠችው ትኩረት ለኢኮኖሚ እድገቷና ልማቷ ውጤታማነት መሰረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋዊ ጉብኝትም ሀገራችን የጀመረችውን የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎችን የሚያጠናክሩ፣ የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጎለብቱ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያሳልጡ ልምዶች መቅሰም አስችሏል፡፡ የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎችንም ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ተሞክሮ አንድ፣ ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠትና በፅናት የታገዘ እልህ አስጨራሽ ርብርብ በማድረግ በአንድ ትውልድ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መዝገብ የሚቻል መሆኑን ከቬየትናም የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ቬየትናሞች ለግብርና ልማት፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነቶችን በማድረግ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበዋል፤ በዚሁ ባለፉት 30 ዓመታት ከ5-7 በመቶ ያልተቋረጠ እድገት በማስመዝገብ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ብዝሃ ሴክተር የኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግራለች፡፡ በአገር በቀል የኢኮኖሚ እቅዷና ሪፎርሟ ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ግንባታዋ አዕማድ ወይም ምሳሶ በማድረግ ባለፉት 7 ተከታታይ ዓመታት ከሰባት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ታሪካዊ ስራ አከናውናለች፡፡ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷንም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡ የቬየትናሞቹ ልምድና ተሞክሮም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ትክክለኛነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቬየትናም የተገኘው ልምድና ተሞክሮ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር በያዘችው መንገድ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቬየትናም ካስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የላቀ እድገት ማስመዝገብ እንደምትችል የሚጠቁም ነው፡፡ ተሞክሮ ሁለት፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የቬየትናም ዜጎች በ1990ዎቹ ዓመታት ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ነበር። ሆኖም ቬየትናም በተከተለችው የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ በተለይም ለግብርና ልማት በሰጠቸው ልዩ ትኩረት በ2020 ይህን አኃዝ ወደ 4% (በመቶ) ዝቅ እንዲል አድርጋለች:: የግብርና ሪፎርሟ ውጤታማ በመሆኑ ራሷን በምግብ ሰብል ከመቻል አልፋ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀጣናው ከፍተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች:: ይህ በጎ ልምድና ተሞክሮም፣ ኢትዮጵያ ተረጅነትን በመቀነስ፣ ራስን በምግብ ሰብል በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለው ሁለንተናዊ ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ አስረጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ አብዮት ራስን ለመቻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሆኗል፡፡ ከዚህ የተገኘውን ልምድ በመውሰድ አሁን ደግሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በሩዝ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ጀምራለች፡፡ በዚህም ረገድ የቬየትናሞች ስኬት ኢትዮጵያ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም የጀመርናቸውን መልካም ስራዎች የሚያጠናክሩ የአገር ውስጥ ልምዶችን ከማጎልበት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ በጎ ልምዶች በመቀመር በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን መነሳሳት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቬየትናም ያሉ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያ ለምትካሂዳቸው የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ተሞክሮ ሶስት፣ ቬየትናም የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በቀጠናው ካሉ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ ሰፋፊ ድርድሮችን አካሂዳለች፡፡ በዚህም ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በየዓመቱ ከ34 ቢሊየን ዶላር በላይ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ችላለች፡፡ ይህም በቀጠናው ከፍተኛ የሚባል የኢንቨስትመን ስበት ማሳያ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ብዙ ርቀት የተጓዘ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ድርድሮቹም ውጤት እየተገኘባቸው መጥቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ነፃ የንግድ ስምምነት ለመፍጠር ከሀገሮቹ ጋር በርካታ ድርጅሮችን እያካሄደች ነው፡፡ ይህም ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡ በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማካሄድ ቬየትናምን ሰፊና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ያስቻሏትን የድርድር መንገዶች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን በመመርመር ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምትፈጽማቸው ስራዎች እንደየሁኔታው መጠቀም ይገባል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቬየትናም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እየተጋረጠባቸው መጥቷል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ፣ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ ርካሽ ጉልበት፣ እየዘመነ የመጣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአንድ ማዕከል ወይም አካባቢ የተሰበሰቡ ኢንዲስትሪዎች መጠናከር እና የነጻ የንግድ እና ኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እንደ ቬየትናም ላሉ ሀገሮችና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት ከዚህ አኳያ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ይህን ምቹ እድል አጠናክሮ መጠቀም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ተሞክሮ አራት፣ ቬየትናሞች ለሰብአዊ ልማት በተለይም ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ የሰጡት ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያቸው ይበልጥ እንዲያድግ ረድቷል:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅባለቸው ከ99 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅበላውም ወደ ዘጠና በመቶ የተጠጋ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በመካከለኛ እድገት ደረጃ ካሉት ሀገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ ቬየትናም በዓለም አቀፉ የሰብአዊ ልማት index መሰረት ከሲንጋፖር ቀጥላ ሁለተኛዋ የሰብአዊ ካፒታል የገነባች ሀገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያም በቅርቡ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትውልድ ግንባታ አቅጣጫን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የቬየትናም ጉብኝትም ከዚህ አኳያ ጠቃሚ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ቬየትናሞች የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ሀብት ልማት ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በየዓመቱ መጠነኛ ቁጥር ላላቸው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አብሮ ለመስራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ይህንኑም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡ በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬየትናም የነበራቸው ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው። የልዑኩም ቆይታ የኢትዮጵያን ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ተሞክሮ ለመቃኘትና የጉዞአችንን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ መጪው ጊዜ አዲስ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት እንዲሆን አቅም የፈጠረ ነው። በቬየትናም የቆይታ ምዕራፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የታደሙበት “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የቬየትናሙ የፒ4ጂ ጉባኤ፣ ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች የታዩበት መሆኑ ታይቷል። የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል። ጉባኤው ለ2027 ለሀገራችን ሌላ እድል አምጥቶና የመሪያችንንና ህዝባችንን ክብር ባረጋገጠ አኳሃን ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታካሂድ ችቦ አረካክቧል። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ቬየትናም በሌላ ምዕራፍ ልምድና ተሞክሮዋን፣ በብዝሃ እምርታና ስኬት ይዛ እንድትቀርብ ለማድረግ ርብርባችንን ከወዲሁ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።
የሀገራችንን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ከመጠበቅ ባለፈ ታሪክን የማደስ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ
Apr 18, 2025 202
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የሀገራችንን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ከመጠበቅ ባለፈ ታሪክን የማደስ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ሀይል አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ከሰላሳ ሰባት ዓመት በላይ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየውንና የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም ይንቀሳቀሱበት የነበረው የDHC-5 Buffalo አውሮፕላንን ጥገናና ማሻሻል በማድረግ ወደ ስራ ላስገቡ ኢንጂነሮችና ቴክኒሺያኖች ምስጋና አቅርበዋል።   አውሮፕላኑ ሙሉ ጥገና የተካሄደለትና ከዘመኑ ጋር የተዋሀዱ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን ማረጋገጣቸውንና በተደጋጋሚ ሙከራ ወደ ሀይል እንዲቀላቀል በመደረጉ መደሰታቸውን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል። አዛዡ፤ በተቋሙ የሚመራመሩና ተአምር የሚፈጥሩ ወጣቶች መኖራቸውን ያየንበትም ነው ሲሉ መናገራቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።   መከላከያ ትጥቆችን ከመግዛት በተጨማሪ አምራች ለመሆን እያደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን የገለፁት አዛዡ፤ አንጋፋው የአየር ሀይልም የዚሁ አካል በመሆን በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል። ለታላቅ ሀገር፣ ታላቅ የአየር ሀይል በሚል መርህ የተገነባው የአየር ሀይል የሀገራችንን የአየር ክልል ከመጠበቅ ባለፈ ታሪኩን እያደሰና ዘመኑን የዋጀ ተግባራትን እያከናወነ ሀገራዊ አቅም የመሆን ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።   በአየር ሀይል ቴክኒሺያኖች ጥገናና መሻሻል ተደርጎለት ወደ ሀይል የተቀላቀለውና የካናዳ ስሪት የሆነው የDHC-5 Buffalo አውሮፕላን የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ከሀገር ሲሸሹ እስከ ኬንያ የሄዱበት አውሮፕላን መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ሲልም መከላከያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ነው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
Apr 18, 2025 206
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግ አጋርነት የተፈጠረበት መሆኑን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ እና ቬይትናም መካከል መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1976 መሆኑን ጠቅሰዋል።   ቬይትናም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምትከተል ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በአየር ንብረት እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በቬይትናም ቆይታቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ውይይቱ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም በዓለም አቀፍ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቬይትናም ደግሞ በኤዥያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየፈጠሩ ያሉ ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ የገበያ እድል እንዲፈጥሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡   ቬይትናም በአምራች ኢንዱስትሪ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የምታቀርብ መሆኗ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ቬይትናም የዓለም ሁለተኛዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ሶስተኛዋ ቡና አምራች ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በስምምነቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ዝርዝር አፈፃፀም ሂደቱን የሚከታተል አካል ለመሰየም መነጋገራቸውንም አምባሳደር ደሴ ገልጸዋል፡፡ ቬይትናምና ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካና ወደ ኤዥያ መግቢያ በር እና አገናኝ ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው፥ ይህም ከሁለቱ ሀገራት ያለፈ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው- አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ
Apr 18, 2025 167
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የግብርና ፕሮግራሞችን በመተግበር የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ። ኢትዮጵያ በብራዚል መዲና ብራዚሊያ በተካሄደው የብሪክስ የግብርና ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፋለች። ብሪክስ ፍትኃዊና ወካይ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ያበረክታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት እየተተገበሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ የተቀናጁ ፖሊሲዎች እና ኢንሼቲቮችን አስመልክቶ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።   የስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኩታገጠም እርሻ፣ የተጎዳ መሬት መልሶ ማልማት እና የመስኖ ኢኒሼቲቮችን ለአብነት አንስተዋል። ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ አመራር እና የተቀናጁ ኢኒሼቲቮች አፍሪካን መለወጥ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የግብርና ፕሮግራሞችን በመተግበር የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትቷን ለማረጋገጥ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል። በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል እና አጋር አገራት ጋር በመሆን በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የእውቀት ማጋራት እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል። አምባሳደር ልዑልሰገድ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስላሉ መጠነ ሰፊ የግብርና እድሎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የብሪክስ የንግድ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉ አማራጮችን በመቃኘት በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማራ ጥራ አቅርበዋል። ከግብርና ሚኒስትሮች ስብሰባ አስቀድሞ የግብርና ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ መካሄዱን በብራዚሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን አድርገዋል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
Apr 18, 2025 212
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ። የኢትዮጵያ እና ቬይትናም ግንኙነት 50 ዓመታትን ማስቆጠሩን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቬይትናም ያደረጉት ጉብኝት በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው የመሪ ጉብኝት መሆኑን ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የልዑካቸው የቬይትናም ጉብኝት ስኬታማ እንደሆነ በማውሳት፥ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ትብብርን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን ጠቅሰዋል።   ከስምምነቶቹ መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቬይትናም በረራ እንዲጀምር የሚያስችለው ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፤ አየር መንገዱ በረራ ሲጀምር የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት፣ የህዝብ ለህዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ያጠናክራል ብለዋል። በትምህርት ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች መደረጋቸውንም አስረድተዋል። በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ምን ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ መከተል እንደሚያስፈልግ ስምምነት ለማድረግ ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል። ይህ እውን ሲሆን ተቋማዊና ዘላቂ የሆነ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።   የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(ፒ4ጂ) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ መመረጧንም አንስተዋል። ዓለም አቀፍ የትብብር መድረኩ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎቿን ለዓለም እንድታሳይ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የታዳሽ ኃይል እንደምትጠቀም አመልክተው፤ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ የታዳሽ ኃይል ልማት እያከናወነች እንደምትገኝ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በዘላቂነት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ለመጠቀም ግልጽ አቋም ይዛ እየሰራች መሆኗንም ገልጸዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ከራሷ አልፎ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ሥራዎች አጋዥና ምሳሌ እንደሆነም ጠቁመዋል።   የፒ4ጂ የትብብር መድረክን ለማዘጋጀት መመረጧም ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ እና ተሰሚነቷ እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል። መድረኩ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ተነሳሽነቶችና ተግባራዊ ስራዎችን ሌሎች ሀገራት በመመልከት በጋራ የመስራት አቋም እንዲወስዱ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል። በአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ላይ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ የግሉ ዘርፍ በቂ ፋይናንስ በማሰባሰብ ሚናውን እንዲወጣ የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ነው የተናገሩት።
መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያጠናክሩ ተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ እየሰራ ነው - የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር)
Apr 17, 2025 201
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያጠናክሩ ተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ እየሰራ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለጹ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት መንግስት ሀገርንና ሕዝብን የሚያገለግሉ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል።   የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን የሚያጠናክሩ እንደ መገናኛ ብዙሃን ያሉ ተቋማትን አቅም የመገንባት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ህገ መንግስታዊ መሆኑን ገልጸው በዚህም መገናኛ ብዙሃን ነጻነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በዘርፍ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም የሕዝብ፣ የግል እና የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በብዛት፣ በቋንቋ እንዲሁም በስርጭት ቁጥራቸው በእጅጉ መጨመሩን ተናግረዋል። ነገር ግን የሃሳብ ነፃነት ባልተገባ መንገድ ሲገለፅና ከህግ ወጪ ሲሆን ደግሞ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፋለጊ እንደሆነም ገልጸዋል።   የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አስመልክቶ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል። በስራ ላይ የነበረው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ የአደረጃጀት፣ የቁጥጥር መላላትና ከአስተዳደር ጋር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ማሻሻያ እንደተደረገበት ገልጸዋል። የባለሥልጣኑ የዕለት ተዕለት ሥራዎች አፈጻጸም፣ የቦርድ አሰያየም፣ የቁጥጥር እና ተጠያቂነት ስርዓት ጋር በተያያዘ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ መሻሻል ማስፈለጉን ተናግረዋል። የተሻሻለው አዋጅ መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እየዘመኑ እንዲሄዱ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በማስተካከል መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡ ማስተዳደር እና መቆጣጠር እንዲቻልም የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ጠቁመዋል። የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የተሻሻላው አዋጅ ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ምህዳር የሚፈጥር በመሆኑ የሚዲያ ነጻነት እንዲተገበር ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም ከሕግ አግባብ ውጪ በሚንቀሳቀሱት ላይ በሀገሪቱ ሕግ መሰረት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል።   በተመሳሳይ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ አህመድ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል። ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የባህር ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው- ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ
Apr 17, 2025 128
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ)፦ የባህር ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ። ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ከክፍሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን እየተገነባ ያለውን የባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያና የባህር ኃይል መሠረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል፡፡ የቢሾፍቱ ባህረኞች ትምህርት ቤት የግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ኢንጂነር መሀመድ ሀሰን የባህር ኃይል የባህረኞች ትምህርት ቤት ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ 24 ሰዓት በትጋት እየተሰራ ነው ብለዋል።   በተመሳሳይ አዲስ አበባ ጃንሜዳ የሚገነባው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ኢንጂነር በቀለ መለሰ የጠቅላይ መምሪያው ቢሮዎች፤ የህክምና አገልግሎት መስጫ ክሊኒክ፤ የስብሰባ አዳራሽ፤ ስቶር፤ የስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶችን ግንባታ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። ለፕሮጀክቱ ጥራት እና ፍጥነት የአመራሩ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።   የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ባህር ኃይሉን ለማጠናከር በመንግስት አስፈላጊው በጀት መመደቡንና በከፍተኛ አመራሩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል። ዋና አዛዡ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በጥሩ ደረጃ እና በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የጅቡቲ ብሄራዊ የሜዳሊያ ሽልማት አገኙ
Apr 17, 2025 90
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የጅቡቲ ብሄራዊ የሜዳሊያ ሽልማት ዛሬ ተበርክቶላቸዋል። አምባሳደር ብርሃኑ ከጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዱልቃድር ካሚል መሀመድ የ “ጁን27 ኦፊሰር ዳንስ ላሬድ ናሽናል ሜዳሊያ” በመቀበሌ እጅግ ደስ ብሎኛል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።   የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በየደረጃው ይበልጥ እንዲጠናክር ላሳዩት ቤተሰባዊ ድጋፍ እና ክትትል ልዩ ምስጋዬን ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል። ጅቡቲ ሁለተኛ አገሬ ናት ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኙነት በጋራ ህዝቦች ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ወዳጅነት እና የዘመናት ወንድማማችነት ያለን ህዝቦች ነን ሲሉ ገልጸዋል።   ለቀጣናው ተምሳሌት የሆነው የሀገራቱ የኢኮኖሚ ትስስር በአህጉራዊ እና አፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው እንደሚቀጥል አመልክተዋል። አምባሳደር ብርሃኑ የጅቡቲ መንግስት በቆይታቸው ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ሞሪኤራ ዳ ሲልቫ ጋር ተወያዩ
Apr 17, 2025 90
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ሞሪኤራ ዳ ሲልቫ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በውይይቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት(UNOPS) የኢትዮጵያ መንግስት በሚያከናውናቸው በተለያዩ የግዢ ሂደቶች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡   የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤቱ በአፍሪካ ውስጥ በሚያከናውናቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን ዕቃ አቅራቢዎችን እንዲያሳትፍና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጽህፈት ቤት እንዲያስፋፋም መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ሞሪኤራ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡   ጽሕፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልግም ጠቁመዋል፡፡
ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይበልጥ መስራት ይገባል - ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)
Apr 17, 2025 92
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የሚፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይበልጥ መስራት እንደሚገባ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች እና አመራሮች በ2017ዓ.ም የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት አድርገዋል።   በመድረኩ የአፈፃፀም ሪፓርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ምርታማነትን እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ያስቻለ ነው ብለዋል። በ2017ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ኢኮኖሚው በ8 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉ የተገለፀ ሲሆን 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ መገኘቱን ገልጸዋል። በዲኘሎማሲ መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከር እንዲሁም በባለብዙ ወገን መድረኮች ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን ማሳደግ እና ጥቅሞቿን ማስጠበቅ ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አምባሳደር ፍፁም አንስተዋል። በዘጠኝ ወሩ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሬሚታንስ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ የተላከ ሲሆን ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 12 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸዋል። መድረኩን በአወያይነት የመሩት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንዳሉት ውይይቱ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ እና እየሄደችበት ያለውን መንገድ ለመገንዘብ የሚያስችል ነው።   ባለፉት ሰባት አመታት የተተገበሩ ሁለንተናዊ የሪፎርም ስራዎች የኢትዮጵያን የእድገት ማነቆዎች ለመፍታት እና ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ ያስቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል። የአለም ሁኔታ ተለዋዋጭነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በመጪው ጊዜ የሚፈጠሩ እድል እና ስጋቶችን በጥልቀት በመመዘን ጥቅማችንን ለማሳደግ መስራት አለብን ብለዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለው የታሪፍ ጦርነት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና የንግድ ስርአት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ በማጤን በቀጣይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተገልጿል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና ለሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ ሚና የምትጫወት መሆኗን ዳግም ያረጋገጠችባቸው ስኬቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት መመዝገባቸው በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።
ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ ነው - ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን
Apr 17, 2025 96
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ገለጸ። በአገር ደረጃ በአፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች 25 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ሂደት ማለፋቸውም ተገልጿል። በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየው የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ዛሬ ዳግም ተጀምሯል። የስልጠና ሂደቱንም የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎች ልዑክ በመቀሌ የስልጠና ማዕከል ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል። የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከትግራይ ክልል በተጨማሪም በአፋር፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎችም የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ተከናውኗል። በትግራይ ክልል ቀደም ሲል ስልጠና ሲሰጥባቸው በቆዩት የመቀሌና ዕዳጋ ሀሙስ የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም የስልጠና ማዕከላት የቀድሞ ታጣቂዎችን ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሚገኙም አስታውቀዋል። አሁን ላይ አምስት ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና እያለፉ ይገኛሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በእስከ አሁኑ ሂደት 12 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና እንዲያልፉ መደረጉን አስታውቀዋል።   በአጠቃላይ እንደ አገር በአፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች 25 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ሂደት ማለፋቸውን አብራርተዋል። የተሀድሶ ስልጠናውም በዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል በተሀድሶ ስልጠና መደበኛ ህይወታቸውን መምራት እንደሚኖርባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍስሀ ኪዳኑ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መነሻነት የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈጸም በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው። የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ የማድረግ ስራም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤ ገባይዴ ዶ በመቀሌ የስልጠና ማዕከል የቀድሞ ታጣቂዎች የዲሞብላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም የስልጠና ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶ ስልጠና ሂደት የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በምልከታው በአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የቁጥጥር፣ ማረጋገጥና ማስከበር ተልዕኮ ልዑክ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሳማድ አላዴ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአጋር የልማት ድርጅቶችና የሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅም እንዲጎለብት አድርጓል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Apr 17, 2025 90
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅሟ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዲጎለብት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወኗም ተገልጿል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰሩ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል። ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት በቀጣናው ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አከናውናለች ብለዋል፡፡ በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል። 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛ የህብረቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በተሳታፊዎች ዘንድ አድናቆት የተቸረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውጤታማ ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ ለ968 ዜጎች ነፃ የትምህርት እድል ማመቻቸት እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ከተለያዩ ሀገራት ጋር 11 ስምምነቶች ተፈርመው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንዲጸድቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከሀምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ገቢራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅምና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዲጎለብት ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሻሻል በሚሲዮኖች በኩል 143 የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በዚሀም 533 ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ምርቶች በ88 የንግድ ማስተዋወቂያ መድረኮች በመሳተፍ 98 አዳዲስ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ92ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ 700 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በቅርቡ ከ130 በላይ ኢትዮጵያውያን ከማይናማር መመለሳቸውን ገልጸው፤ በቀጣዮቹ አስር ቀናትም 200 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድርግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
Apr 17, 2025 73
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡- በመዕራብ ኦሞ ዞን የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የጋራ ትብብር እና ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ በምዕራብ ኦሞ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የፀጥታ ሥራዎችን ገምግመዋል። በውይይቱ ላይ ከዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በዞኑ ከፌደራል ጀምሮ የነበረው የፀጥታ አካላትና አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በተከናወነው ሥራ የተሻለ ሰላም በአካባቢው መስፈኑን ገልጸዋል። የተጀመረው የጋራ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለዘላቂነት መረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል። ሌተናል ጀነራል አስራት ዲኔሮ፥ በዞኑ ሲሰሩ የነበሩና የተገኙ ውጤቶችን ያነሱ ሲሆን አመራሩ፣ህዝቡና የፀጥታ በማጠናከር አሁን የተገኘውን ውጤት ማላቅ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ፥ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ቁጥጥርን ጨምሮ በቀጣናው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፥ ለዚህም የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ጀነራል መኮንኑ ማህበረሰቡ ሰላም ለማስከበር እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ከፌደራል እስከ ወረዳ ያለው የፀጥታ አካላትና አመራሩ በመቀናጀት በዞኑ የመጣው ሠላም ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። በሂደቱ የተሳተፉ እና የድርሻቸውን የተወጡ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ አሁን የመጣው ውጤት ዘላቂ ለማድረግ የህግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። ህገወጥ የጦር መሣሪያ ምዝገባና ቁጥጥር እንዲጠናከር፣በማዕድን አካባቢና በወረዳዎች መካከል በወሰን አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በወንድማማችነት እና በመተጋገዝ መንፈስ መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ችግሮችን አመራሩ የፀጥታ አካላትና ህዝቡ በመቀናጀት መፍታት እንደሚገባው አመልክተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ የብልፅግና ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች በተቀመጠው አግባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አመራሩና የፀጥታ መዋቅሩ ለውጤታማነት እንዲተጋ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየው የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ተጀመረ
Apr 17, 2025 85
መቀሌ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየው የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ዳግም ተጀምሯል። የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎችና ተወካዮች ለቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች የሚሰጠውን የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም የስልጠና ሂደት ተመልክተዋል።   በምልከታው ላይ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍስሀ ኪዳኑ፣ በአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የቁጥጥር፣ ማረጋገጥና ማስከበር ተልዕኮ ልዑክ ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ሳማድ አላዴ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአጋር የልማት ድርጅቶችና የሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል። የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ተቋርጦ ቆይቷል። በመሆኑም የቀድሞ ታጣቂዎችን የማረጋገጥ፥ ዲሞቢላይዝ የማድረግ፥ የመመዝገብና የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ዳግም ዛሬ በመቀሌ የተሃድሶ እና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ማዕከል ተጀምሯል። በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን የዲሞብላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ህዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች -ኢንጂነር አይሻ መሀመድ
Apr 17, 2025 83
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር ያላትን የቆየ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ። የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፥ ከተሰናባቹ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ /ICRC/ ልዑካን ቡድን መሪ ብሩስ ሎሪየንዝን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የቀይ መስቀል ኮሚቴው ባላቸው ትብብር እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፥ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ከኮሚቴው ጋር በቅርበት ለመስራት ምንግዜም ቁርጠኛ ናት ብለዋል። ተሰናባቹ የኮሚቴው ልዑካን መሪ ብሩስ ሎሪየንዝን በበኩላቸው፥ በቆይታቸው የመከላከያ ሚኒስቴር ለሥራቸው ላደረገው ትብብር እና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ የአሰራር ድንጋጌዎችን በማክበር እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል። በዚሁ ወቅት አዲስ የተሾሙት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑካን መሪ ሲሞኔ ካሳቢያንካ ከሚኒስትሯ ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Apr 17, 2025 121
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰሩ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለጎረቤት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ በዚህም ከጎረቤት ሀገር ጋር ያላትን ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። በየካቲት ወር የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በልዩ አድናቆት የታየ እንደነበር አመላክተዋል። በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸው፥ ለአብነትም 968 የሚሆን ነጻ ከፍተኛ የትምህርት እድል ማመቻቸት መቻሉን ጠቁመዋል። ከተለያዩ አገራት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ጋር በተያያዘም 11 ስምምነቶች ለምክር ቤት ቀርበው መጽደቃቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅምን በማሳደግ ተጽእኖ ፈጣሪነቷ እንዲጎለብት ማስቻሉን ገልጸዋል። በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ 92 ሺህ በላይ ዜጎች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም