ማህበራዊ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
Apr 21, 2025 81
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ):- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ሊቀ መንበሩ በሀዘን መግለጫ መልዕክታቸው ፖፕ ፍራንሲስ የዘመናችን ግዙፍ የሞራል መገለጫ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ለሰላም፣ ፍትህ፣ መልካምነት እና ለመንፈሳዊ መሪነት በጽኑ ሲተጉ የነበሩ መሪ ናቸው ብለዋል። ፓፕ ፍራንሲስ ለሰላም በነበራቸው ጽኑ መሻት፣ ለተቸገሩ ወገኖች በሰጡት ትህትና የተሞላበት አገልግሎት፣ በአየር ንብረት ለውጥ በነበራቸው ጠንካራ ተሟጋችነት እንዲሁም የተለያየ ባህልና እምነት ባላቸው ማህበረሰቦች መካከል ምክክር እንዲኖራቸው በነበራቸው ትጋት ሁሌም ሲታወሱ እንደሚኖሩ አመልክተዋል። በአፍሪካ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን፣ ሰላም እና እርቅ እንዲፈጠር እንዲሁም በግጭት እና ድህነት ከተጎዱ ሰዎች ጎን በመቆም ያሳዩትን አጋርነት አድንቀዋል። ሊቀ መንበሩ ለሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እና በጎ ስራቸውን ለተከተሉ ሰዎች በሙሉ ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህይወታቸውን ሙሉ ለጌታና ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ታላቅ እረኛ ነበሩ - ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል
Apr 21, 2025 79
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 13/2017 (ኢዜአ):- የሮማ ካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ ህይወታቸውን ሙሉ ለጌታና ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ ታላቅ እረኛ ነበሩ ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ88 ዓመታቸው በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ቫቲካን አስታውቃለች፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህልፈትን አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ ሰጥተዋል።   በመግለጫቸውም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን እኝህን ታላቅ አባት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ማግስት ወደዘላለማዊ ማረፊያው ወስዷቸዋል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ባለፉት ወራት ባደረባቸው ከባድ ህመም ህክምና ሲከታተሉ እንደነበር በማውሳት፥ ትናንት በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት የትንሳኤን በዓል እና ለዓለም ሰላም የመልካም ምኞት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ዛሬ ጠዋት የቅድስት መንበር እረኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን በመስማታችን ከባድ ሀዘን ተሰምቶናል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህይወታቸውን በሙሉ ለጌታና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እረኛ እንደነበሩም ገልጸዋል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በክህነት፣ በሊቀ-ጳጳስነት፣ በካርዲናልነት እንዲሁም በቅድስት መንበር እረኝነት በርካታ ሐዋሪያዊ አገልግሎቶችን ያበረከቱ አባት እንደነበሩም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የሀዘንና የሥርዓተ ቀብር መርሃ ግብሮች በቀጣይ ይፋ እንደሚደረጉም ተናግረዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እ.አ.አ ታኅሣሥ 17 ቀን 1936 በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ ነበር የተወለዱት።
የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
Apr 21, 2025 58
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ እንዲሰማሩ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ጥሪ አቀረቡ። በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሀ ሻውል የተሳተፉበት የእስያ የቢዝነስ እና ሶሻል ፎረም ተካሄዷል። ፎረሙ ከአፍሪካ፣ አሜሪካና እስያ የተወጣጡ ባለሀብቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ ያገናኘ ሲሆን የዓለምን የቢዝነስ ስነ ምህዳር ላይ ለውጥ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።   በመድረኩ ላይ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ኢትዮጵያ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና የአፍሪካ መግቢያ በር ናት ብለዋል። መንግስት የተለያዩ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ የወሰዳቸውን እርምጃዎች አስመልክቶም ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። የኢኮኖሚ ኢኒሼቲቩ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተለይም በጤና ክብካቤ እና የጤና ቱሪዝምን ለመሳብ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ለጤና አገልግሎት የሚመርጧት ዋንኛ መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት። የህንድ ባለሀብቶች ይህን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ እና የጤና ቱሪዝም መስኮች ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል። ፎረሙ ለዜጎች እና ተቋማት ዘላቂ ሀብት መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ለውጦች፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢነርጂ ሽግግር ላይ ትኩረት በማድረግ መወያየቱን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ
Apr 21, 2025 40
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ህይወት መሐመድ ገለፁ። የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽንና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።   ስምምነቱን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሐመድ እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) ፈርመውታል። ስምምነቱ በባህልና ስፖርቶች ጥናትና ምርምር ለማከናወን እንዲሁም፣ በባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ህይወት መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ፌዴሬሽኑ የባህል ስፖርትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር አየሰራ ነው። ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት በርካታ የባህል ስፖርቶችን ለማጥናት እና ለማሳደግ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።   የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በእውቀት እና ክህሎት ብቁ መምህራን እና የትምህርት አመራሮችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ስምምነቱ የሀገሪቱን የባህል ስፖርቶች ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሃለፊነት በአግባቡ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራንን አቅም መገንባት ተችሏል - ትምህርት ሚኒስቴር
Apr 21, 2025 59
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራንን አቅም መገንባት እንደተቻለ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሀገር የሚገነባ ትውልድ መፍጠር የሚያስችለውን ሀገር አቀፍ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተጀመረው ንቅናቄ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቷል፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችል የተሳለጠ የመማር ማስተማር ሥርዓት ተፈጥሯል። በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር በአጠቃላይ የትምህርት ስርአቱ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ በመገንዘብ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ፣ እንዲሁም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ግባቸው ብቁና አምራች ዜጋ መፍጠር የሚያስችል የተሳለጠ የመማር ማስተማር ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ82 ቢሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ አካላት ሀብት በመሰብሰብ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል ብለዋል፡፡ ንቅናቄው በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንዲሁም በቂ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ማቅረብ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ጊዜያቸውን በትምህርት ቤቶች ማሳለፍ እንዲችሉ የተሟላ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ ወንበሮችና ሌሎች ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ንቅናቄው ትምህርት ብዙ ሀብት የሚጠይቅ መሆኑንና ከመንግሥት ባሻገር የግሉ ዘርፍ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራንን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የመምህራንን ብቃትና ተነሳሽነት ለማሳደግ የመምህራንና ትምህርት ቤቶች አመራር ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ መምህራን በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ላይ በቂ መረዳትና እውቀት ኖሯቸው ተማሪዎችን ማብቃት የሚችሉበት እድል መፈጠሩን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ የተማሪዎች ምገባ ስርዓት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት የሚከታተሉበት እድል ተፈጥሯል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ምገባው ለወላጆች እፎይታን በመስጠትና የሥራ ዕድል በመፍጠር መልከ ብዙ ጥቅሞች ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የመኖሪያ ቤቶችን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ
Apr 21, 2025 44
ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በተለይም በከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት አይመጣጠንም። ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ በቀለ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል መንግስት በራሱ አቅም የሚያከናውናቸው ተግባራት፣ በግሉ ሴክተር ተሳትፎ፣ በማህበራትና በበጎ ፈቃደኞች መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል። በዚህም በክልሉ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቃለል በ2017 በጀት ዓመት ከ129ሺህ 900 በላይ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ከቤት ኪራይ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታትም ብዙ ስራ መሳራቱን ገልጸዋል። በተለይም ቢሮው የአከራይና ተከራይ መብት ሚዛናዊ በሆነ መልክ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ በክልሉ አስፈላጊ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል። በዚህም መሰረት ከተከራይና አከራይ ስምምነት ውጪ አከራይ ተከራይን እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ከተከራየው ቤት ማስወጣትም ሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንዳይችል መደረጉን ገልጸዋል። በመመሪያው መሰረት እስከሁን ከ117ሺህ 900 በላይ የመንግስት ቤቶች እና 148ሺህ በላይ የግል የኪራይ ቤቶች ውል በአሰራሩ ተመዝግቧል ብለዋል።
ፖሊስ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከ146 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን ገለጸ
Apr 21, 2025 55
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከ146 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታውቋል፡፡ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል በተደረገ ኦፕሬሽን፤ 121 የጦር መሣሪያዎችን ከመኖሪያ ቤቶች፣ 8 ሺህ 989 ከፀረ-ሰላም ኃይሎች እና 36 የጦር መሣሪያዎችን በኬላዎች ላይ መያዙን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም 6 ሺህ 351 የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶች ከመኖሪያ ቤቶች፣ 8 ሺህ 989 ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 51 ሺህ 846 በኬላዎች እንደተያዙ የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያሳያል። እንዲሁም 236 የተለያዩ የጦር መሣሪያ ካዝናዎች በመኖሪያ ቤቶች እና 148 በኬላዎች ላይ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ 1 ብሬን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 2 ብሬን በኬላዎች የተያዘ ሲሆን፤ 31 የተለያዩ ቦምቦች ከመኖሪያ ቤቶች፣ 25 ቦምቦችን ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 122 ቦምቦችን በኬላዎች መያዙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ 32 የተለያዩ ሕገ-ወጥ ሽጉጦች ከመኖሪያ ቤቶች፣128 ሽጉጦች ከፀረ-ሰላም ኃይሎች፣ 102 በኬላዎች መያዝ መቻሉንም ፖሊስ ጠቅሷል። 1 ስናይፐር ከመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም 1 ስናይፐር ከፀረ-ሰላም ኃይሎች በኤግዚቢትነት መያዙን እና 146 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድቷል፡፡ ሕብረተሰቡ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ሲመለከት በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአስተዳደሩ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን የኑሮ ደረጀ የሚያሻሽሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው
Apr 21, 2025 66
ሰቆጣ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቀሚዎችን ከተረጂነት ማውጣት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የአስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት አስታወቀ። የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለኢዜአ እንደገለፁት አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ ህብረተሰቡ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በሴፍቲኔት ፕሮግራም ያማገዝ ሥራ እየተሰራ ነው። በአስተዳደሩ ከሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ውስጥ በአሁኑ ዙር 55ሺህ 362 የሚሆኑትን ከተረጂነት ለማላቀቅ ታቅዶ እየሰራ ነው። ዘንድሮም በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር 217 ሚሊዮን 470ሺህ ብር በመመደብ 12ሺህ 300 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በተለያዩ የልማት ዘርፎች የማሰማራት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም በአስተዳደሩ ለሚገኙ 400 እማወራና አባወራዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በ16 ሚሊዮን ብር የውሃ መሳቢያ ጀነሬተር በመግዛት ማሰራጨቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም 1ሺህ 204 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ ቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ለእያንዳንዳቸው 33 ሺህ ብር እንደተሰጣቸው አስረድተዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው ተጠቃሚዎችም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች የስራ ዘርፎች ፈጥነው ወደ ስራ በመግባት ኑሯቸውን በዘላቂነት እንዲቀይሩ በየደረጃው ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። ከአስተዳደሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሞገስ ቸኮለ እንዳሉት በተደረገላቸው የውሃ መሳቢያ ሞተር አንድ ሄክታር መሬት የሚደርስ መሬታቸውን በመስኖ ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይ በተደረገላቸው ድጋፍ በምግብ ራሳቸውን በመቻል ኑሯቸውን ለማሳደግ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ኪሮሱ ወናይ በበኩላቸው በተደረገላቸው የውሃ መሳቢያ ሞተር ከልጆቻቸው ጋር በመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በብሄረሰብ አስተዳደሩ በአጠቃላይ 151ሺህ 869 የህብረተሰብ ክፍሎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
Apr 21, 2025 45
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሀመድ እና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) ፈርመውታል። ስምምነቱ በባህል ስፖርቶች ጥናትና ምርምር፣ ትምህርትና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሀመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የሁለትዮሽ ስምምነቱ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የባህል ስፖርቶችን ለማጥናት እና ለማሳደግ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ ለማድረግ ነው። እንዲሁም ባህላዊ ስፖርቶችን በማጥናት በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ለማስፋፋት ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል። የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቀደ ቱሊ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በእውቀት እና ክህሎት ብቁ መምህራንና የትምህርት አመራሮችን እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የሀገሪቱን ባህላዊ ስፖርቶችን ለማሳደግ ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የትንሳኤ በዓልን ጤና ባለሙያዎች እና ታካሚዎች ጋር አከበሩ
Apr 20, 2025 164
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ):-የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እና ታካሚዎች ጋር የትንሳኤ በዓልን አክብረዋል። ዶክተር መቅደስ የጤና ባለሙያዎችን ያበረታቱ ሲሆን ለታካሚዎችም ስጦታ አበርክተዋል። ሚኒስትሯ የጤና ሙያ ራስን ሰጥቶ ህብረተሰቡን ማገልገል ዋንኛ መገለጫው ነው ብለዋል። ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ጎን ለጎን የጤና ባለሙያውን ሕይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀየር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዶክተር መቅደስ ዳባ ከሌሎች የሚኒስቴሩ አመራሮች ጋር በመሆን በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ተገኝተው ማዕድ በማጋራት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሚኒስትሯ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ የአልትራሳውንድ ማሽን ድጋፍ አበርክተዋል። ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ወላጅ አልባ ህጻናትን እና አረጋዊያንን ከወደቁበት አንስቶ ከመደገፍ ባሻገር ራሳቸዉን ችሎ ለሌሎችም እንዲተርፉ ከማድረግ አንጻር አርአያ በመሆን እያከናወነ ላለው ስራ ምስጋና አቅርበዋል። የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ሲሰተር ዘቢደር ዘዉዴ በበኩላቸው ሚኒስትሯ ላደረጉት የአልትራሳውንድ ማሽን ድጋፍ ምስጋና አቅርበው መሳሪያው ዘመኑ የደረሰበትን የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። ሜሪጆይ ኢትዮጵያ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኝ ማዕከሉ ከ4 ሺህ በላይ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 67 ሺህ በላይ ወላጅ አልባ ህጻናትና አረጋዊያንን በመደገፍ አስፈላጊ እንክብካቤ እያደረገላቸው እንደሚገኝ መግለጻቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በሠራተኞች ትጋት የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Apr 20, 2025 100
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ) :-በሠራተኞች ትጋት የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በካዛንቺስ ለሚገኙ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ማዕድ አጋርተዋል። ከንቲባዋ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው፥ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ቀን ከሌሊት በመትጋት ከተማዋ ውብ ገጽታ እንድትላበስ ስላደረጉም ምስጋናቸውን ገልጸዋል። በዓልን በሥራ ላይ ካላችሁ የኮሪደር ልማት ሰራተኞች ጋር ማሳለፍ የስራ ባህል ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የራሱ የሆነ አወንታዊ ሚና አለው ሲሉም ነው የጠቀሱት። በእናንተ ትጋት የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እየተጠናቀቀ ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ የስራ ባህልንም የሚቀይር ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል። በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተመዘገበው ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ገጽታ እየለወጠ መሆኑን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፥ ለሥራ፣ ለመኖሪያና ለመዝናኛ ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር ማድረጉንም ተናግረዋል። በካዛንቺስ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመው፥ ለዚህ ስኬት የሠራተኞች ትጋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ከተማ አስተዳደሩ ለዚህም ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል። በአዲስ አበባ ካዛንቺስ ለወራት በኮሪደር ልማት ሥራ የተሳተፈው ወጣት ሺፈራው ሌዳሞ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት በኮሪደር ልማት ስራ ላይ በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል። በካዛንቺስ የሚገኘው የሴቶች አደባባይ ኮሪደር ልማት ላይ መሳተፉን የጠቀሰው ወጣቱ አደባባዩ እጅግ ተውቦ በማየቱ መደሰቱንም ተናግሯል። ሌላው የኮሪደር ልማት ሰራተኛ ወጣት ወማ ቱንሲሶ በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን የከንቲባ አዳነች ድጋፍና ክትትል ትልቅ ሚና መጫወቱን ጠቅሷል። በዛሬው ዕለትም ከንቲባዋ በዓልን ከኛ ጋር በማሳለፋቸው ደስታ ተሰምቶኛል ሲሉም ሀሳቡን አካፍሏል።
የትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት እየተከበረ ነው
Apr 20, 2025 104
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ) :- የትንሳኤ በአል በኢትዮጵያ በውብ አልባሳት በመድመቅ በባህላዊ ምግቦች ዝግጅት ታጀቦ፣ ጎረቤት ተጠራርቶና ዘመድ ተሰባስቦ የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው። ከእለተ ፋሲካ ቀደም ብሎ ፀሎተ ሃሙስ ከተከናወነ በኋላ እለተ አርብ ደግሞ ስቅለት በመሆኑ በስግደትና ፀሎት ይታሰባል፤ በእነዚህ ቀናት የበዓል ገበያ የእርድ እንስሳና የፍጆታ ምርቶችም ይሸመታሉ። እለተ ፋሲካ እሁድ እለት በደማቅና በሚያምር ድባብ በየቤቱ በሚከናወን ድግስ ከረጅም ጊዜ ፆም በኋላ በርካቶች ስጋን ጨምሮ የእንስሳት ውጤቶችን በመመገብ በዓሉን በደስታ ያከብራሉ። የፋሲካ በዓል ጥልቅ ሃይማኖታዊ ትንታኔ የሚሰጠውና በጥብቅ ዲስፕሊን የክርስቶስን ፍቅርና ለሰው ልጆች የዋለውን ውለታ በማሰብ የሚከናወን መሆኑም ይታወቃል። ከኢትዮጵያም ውጭ በተለያዩ አገራት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን የኒውዝላንድንና አውስትራሊያን ብናነሳ እለተ ፋሲካ በተለይም በመስቀል ቅርፅ የተሰሩ ጣፋጭ ዳቦዎችን በብዛት መመገብ የተለመደ መሆኑ ይነገራል። በደቡብ ፓስፊክ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ የእምነቱ አባቶች እንዲሁም ምእመኑ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ያከብራሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የፋሲካ በዓል በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከበር መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያን በጎነትን በማሳየት፣ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በጋራ ተሰባስቦ በመብላትና በመጠጣት በታላቅ ድምቀት አክብረዋል። በደቡብ አፍሪካ የፋሲካ በዓል የቤተሰብ መሰባሰቢያ ታላቅ የደስታና የአብሮነት ማሳያ በዓል እንደሆነ ይነገራል። በናይጀሪያ እና ማዳጋስካር ደግሞ የመስቀሉን ሃይል የሚያሳዩ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማንሳትና በማብራራት ነው የሚያከብሩት። የትንሳኤ በዓል በአህጉረ ኤዥያዋ ፊሊፒንስ ከማለዳው የምሮ ክርስቶስን በማሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህ እለት ወንዶች የክርስቶስን ምስል ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን ጉዞ በማድረግ እና ሴቶችም ተሰባስበው በተመሳሳይ ሁኔታ ጥቁር ልብስ በመልበስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን በማውሳት ወደ ቤተክርስቲያን በመጓዝ በጋራ ያከብሩታል። በአውሮፓ አገራትም የፋሲካ በዓል አከባበር የካበተና የቆየ ታሪክ ያለው ሲሆን በተለይም በሮማኒያ፣ ሰርቢያ እና ግሪክ የጁሊያን ካላንደርን በመከተል በሌሎች ዓለማት ከተከበረ ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንት በኋላ ነው የሚያከብሩት። በጀርመንም የፋሲካ ዛፍ የሚሉትን በተለያዩ ቀለሞች ባሸበረቁ እንቁላሎች በማስዋብ የሚያከብሩ ይሆናል። በፖላንድም እሁድ ማለዳ ላይ “ባባካ” እያሉ የሚጠሩትን ጣፋጭ ዳቦ በመመገብ በዓሉን ማክበር እንደሚጀምሩ ይነገራል። በብራሰልስም በጎ ፈቃደኞች በሽዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን በመጥበስና ኦምሌት በመስራት ትልቅ ማእድ አድርገው በጋራ በመመገብ ነው የሚያከብሩት። በአሜሪካ እና በሌሎችም ዓለማት የፋሲካ በዓል ከመንፈሳዊ ስርአቱ በሻገር በየአገራቱ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን በማከል የሚያከብሩት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተጠቀሱት አገራትና በሌሎችም በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም