ሳይንስና ቴክኖሎጂ - ኢዜአ አማርኛ
ሳይንስና ቴክኖሎጂ
በዲጂታል መሰረተ ልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
Apr 17, 2025 220
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፡- በዲጂታል መሰረተ ልማት የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ በዲጂታል መሰረተ ልማት እና ስታርት አፕ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገትን ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዲጂታል መሰረተ ልማት አዳዲስ እድሎችን የሚያመጡ ስታርት አፖች፣ ኢ -ኮሜርስና ዲጂታል መታወቂያ ውጤት እያስገኙ ነው፡፡ የዲጂታል መሰረተ ልማት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች፣ ሸማቾች፣ የቢዝነስ ባለቤቶችን እና ሌሎችን በአንድ ላይ የሚያገናኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የዲጂታል መሰረተ ልማተ ዝርጋታ የተሳለጠ ንግድ ሥርዓትን መገንባት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል አስችሏል ብለዋል፡፡ ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቸ ስነ ምህዳር በመፍጠር መንግስት ለዲጂታል መሰረተ ልማት ያወጣውን ወጪ መተካት የሚያስችል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን እውቀትና ክህሎት ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈው ወደ 2ኛ ደረጃ ከተሸጋገሩ 92 ስታርት አፖች መካከል እስከ 700 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2018 የስታርት አፖች ሀብት ግምት ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፤ ካሉት ከሁለት ሺህ በላይ ስታርት አፖች የ513ቱ ብቻ ከ303 ሚሊዮን ዶላር መሻገሩን ገልጸዋል፡፡ በዲጂታል መሰረተ ልማት ከ30 ሺህ 422 በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ በዘርፉ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እውቀትን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ካምፓኒዎችን መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በፈጠራ የታገዘ ችግር ፈቺ ኢንዱስትሪዎችን እንደምትፈልግ የገለጹት ዶክተር ባይሳ ፤ ለዚህ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በምርምርና ልማት መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡ በዚህም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎችን በራሳችን የሰው ሀይል መተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተፈጠረ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ እቃዎች በሀገር ውስጥ ምርት እየተተኩ መሆኑን አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለወረቀት በዓመት እስከ 44 ቢሊዮን ብር ታወጣ እንደነበር አስታውሰው፤ ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምርምር ሥራ ተከናውኖ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል፡፡
አፍሪካ በዌልዲንግ ዘርፍ ያላትን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሀገራት የጋራ ስራ ሊጠናከር ይገባል
Apr 17, 2025 139
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-አፍሪካ በዌልዲንግ ዘርፍ ያላትን ትልቅ አቅም ለመጠቀም የሀገራት የጋራ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ የፌዴራል ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡ ከሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ዓመታዊ ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሄዷል። በመርሃ-ግብሩ ላይ የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አቡደል አሊም፣የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የፌዴራል ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥ ጉባኤው ስኬታማ ነበር። በጉባኤው ለዌልዲንግ ዘርፍ ስኬታማነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ፍሬያማ ውይይቶች የተደረጉበት እንዲሁም አፍሪካ በብየዳ ሙያ ያላትን ትልቅ አቅም ያሳየችበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ትስስራቸውን በማጠናከር ዘርፉን በጋራ ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡበት ነው ብለዋል። የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አቡደል አሊም፥ ኢትዮጵያ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ ጉባኤውን በተደራጀ ሁኔታ በማዘጋጀቷ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ጉባኤው በአህጉሪቱ ስላለው የዌልዲንግ አቅም ግንዛቤ የተፈጠረበት፣ ዘርፉን ለማጠናከር ትምህርት የተገኘበትና በጋራ መስራት እንደሚገባ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በጉባኤው አፍሪካውያን የዌልዲንግ ልምዳቸውን የተለዋወጡበትና በዘርፉ ተጨማሪ እውቀት የቀሰሙበት መሆኑን የተናገረችው በጉባኤው የተሳተፈችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ኮንፊዲ ሎኮንዴ ናት፡፡ ጉባኤው የዌልዲንግ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በኩል ወሳኝ እንደነበር በማንሳት፥ ኩባንያዎች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት እንዲሰሩም ጠይቃለች። በጉባኤው በተካሄዱ ውድድሮች ያሸነፉ ግለሰቦች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፥ አራተኛውን የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤ ደቡብ አፍሪካ እንደምታስተናግድ ታውቋል።
የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
Apr 16, 2025 176
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8/2017(ኢዜአ)፦የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የለውጡ መንግስት የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ተግብሯል ብለዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና የዲጅታል ክህሎትና ልህቀትን በመፍጠር ለአካታች ልማት ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት ያመጣችው ለውጥ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ነው ያሉት። ሀገራዊ የመረጃ ቋት በማዘጋጀት የተሻለ የመረጃ ልውውጥ ለመፍጠር የተጀመሩ ተግባራትን የማፋጠን ሥራ ይከናወናል ብለዋል። መንግሥት ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዲጂታላይዜሽን ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፥ አገልግሎትን ቀልጣፋ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃፅዮን በበኩላቸው፥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣የኤክስፖርትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም የመንግስት ገቢን ከማሳደግ አንፃር ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ አበረታች ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል። ዲጂታላይዜሽንን በሁሉም ዘርፎች እውን የማድረግ ሥራዎች ውጤታማና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ብለዋል።
ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተጠናቀቀ
Apr 16, 2025 152
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተጠናቋል። ከሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤና አለም አቀፍ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሄዷል። በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አቡደል አሊም፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። በሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና አለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአገራቱ መካከል የልምድ ልውውጥ የተደረገበት መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል። የአፍሪካ ዌልዲንግን በተመለከተ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት መደረጉም ታውቋል። አፍሪካ በዌልዲንግ ዘርፍ ያላት ከፍተኛ አቅም የተዳሰሰ ሲሆን ሀገራት ዘርፉን ለማሳደግ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ የተደረገበት መሆኑ ተጠቁሟል። ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው ዓድዋ ድል መታሰቢያ እና አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከልን ጨምሮ የተለያዩ በከተማው የተሰሩ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸው ተገልጿል። በዌልዲንግ ክህሎት ተወዳድረው አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ተበርክቷል። አራተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ ታውቋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ሃይለማርያምን አውሮፕላን ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት በሁሉም መስክ ውጤታማ ስራ የማከናወን ማሳያ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Apr 16, 2025 173
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2017(ኢዜአ)፦ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አውሮፕላን ከ37 ዓመታት በኋላ ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት በተቋሙ በሁሉም መስክ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ። ከአገልግሎት ውጪ የነበረውን የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ሃይለ ማርያም አውሮፕላን ጠግኖ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ ተገልጿል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንደገለጹት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ሃይለማርያም አውሮፕላን ከተጣለበት ጥሻ በማንሳት አፕግሬድና ኦቨር ሆል በማድረግ ከ37 ዓመት በኋላ የበረራ አገልግሎት እንዲሠጥ ማድረግ ተችሏል። ይሄም በመከላከያ ሰራዊት ተቋም ውስጥ በሁሉም መስክ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። አውሮፕላኑ አስፈላጊውን ጥገና አግኝቶ መብረር እና ወደ ኃይል መመለስ እንዲችል በሰጠነው መመሪያ መሠረት ለተሳተፋችሁ የአየር ሃይል አመራሮች ቴክኒሺያኖች የመከላከያ ድጋፍ ሰጪ ሁሉ አመሠግናለሁ ብለዋል። የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው አየር ሃይል በሰው ሃይል ግንባታ ፣ትጥቆችን ማሣደግና ከዘመኑ አቅም ላይ ማድረስ፣ መሠረተ ልማቶችን ተቋሙን በሚመጥን ልክ ማስፋፋት ትኩረት የተሠጠባቸው መሠረታዊ ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸዋል። አውሮፕላኑን ጠግኖ ወደ ኃይል መመለስም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል። ዳሽ ፋይፍ ወይም ቡፋሎ በሚል መጠሪያ የሚታወቀውና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም አገልግሎት ይሠጥ የነበረውን አውሮፕላን ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ አስፈላጊውን ጥገና በአየር ሃይል ቴክኒሺያኖች በመሥጠት ከሰላሣ ሰባት ዓመታት በኋላ ለበረራ ማብቃት እንደተቻለም ተናግረዋል። ለትራንስፖርት ፣ለፓራሹት ዝላይ እና የካርጎ አገልግሎት መሥጠት የሚችለው አውሮፕላን ተጠግኖ ወደ ኃይል እንዲመለስ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ለሠጡት ድጋፍ ሙያተኞች ላደረጉት አበርክቶ ዋና አዛዡ ማመስገናቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሃኖይ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ጎበኙ
Apr 16, 2025 91
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሃኖይ እየተገነባ የሚገኘውን ትልቅ የዘመነ ከተማ (የስማርት ሲቲ) ፕሮጀክት ጎብኝተዋል። ይኽም ለኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራ የሚሆን ተሞክሮ የመቅሰም ተግባር አካል መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጉብኝቱ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶችን ለማላቅ የሚደረግ ፍላጎትና ጥረትን እንደሚያሳይ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
Apr 16, 2025 70
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የጀመረችው ሪፎርም በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ማስቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ። የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትሮች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት እየተገመገመ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የለውጡ መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ተግብሯል። በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን አንስተዋል። የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ በርካታ ውጤቶችን እያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። ለአብነትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል። አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። እነዚህ ስራዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችለዋል ነው ያሉት። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በበኩላቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል። በመድረኩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን በመገምገም በቀጣይ ሦስት ወራት በትኩረት የሚሠሩ ተግባራት ላይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል።
የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ ነው - አቶ ጌቱ ወዬሳ
Apr 16, 2025 81
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8 /2017(ኢዜአ)፦የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አበርክቶው የጎላ መሆኑን የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለፁ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ከሐረሪ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር በፋይዳ መታወቂያ ዙሪያ መክሯል። የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት በብልፀግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት ፋይዳ ዜጎች ወጥ ማንነት እንዲኖራቸው በማስቻል የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ከዜጎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ሙስናን በመከላከል የዜጎችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል። በተለይ የማጭበርበር ወንጀሎችን በማስቀረት የፋይናንስ ዘርፍ ደህንነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል። የፋይዳ መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዙ ግቦችን በማሳካት አበርክቶው የጎላ መሆኑንም ነው የገለፁት። በቀጣይም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አገልግሎት ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚሰራ አክለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ምክትል ሀላፊ አቶ ኦላና አበበ በበኩላቸው ፋይዳ መታወቂያ የአገሪቱን ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለይቶ ለማወቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያግዝ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዜጎች አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ስለመሆኑ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ከ7ሺህ 3 መቶ በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል - የሀረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ
Apr 16, 2025 82
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ከ7ሺህ 3 መቶ በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸውን የሀረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሀላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም ገለፁ። የኤጀንሲው ሀላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም የኮደርስ ስልጠናው የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማዳበር እንደሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። እስካሁን በኢኒሼቲቩ በተሰራው ስራ በክልል ደረጃ ስልጠናውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል 3ሺህ የሚሆኑት የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል። በመርሀ ግብሩ ፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ አንድሮይድና ተያያዥነት ያላቸው ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙም መግለጻቸውን ከክለሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ሥልጠናው ወጣቶችን የክህሎት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ፣ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል። ስልጠናው ወጣቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል በሆኑ ስልጠናውን ያልወሰዱ በቀጣይ ግዜያት እንዲመዘገቡ እና እንዲሰለጥኑ ሀላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል። በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ9ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አቶ ጀማል ኢብራሂም ገልጸዋል። https://ethiocoders.et/
ኢትዮ ኮደርስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማስታጠቅ የአሰራር ስርዓትን ያዘምናል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
Apr 15, 2025 114
አርባ ምንጭ፤ ሚያዚያ 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ኮደርስ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በማስታጠቅ የአሰራር ስርአትን የሚያዘምን በመሆኑ ለስኬታማነቱ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስገነዘቡ። ክልል አቀፍ የኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ አፈጻጸም ግምገማና የንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት ዲጂታል ማህበረሰብን መፍጠር የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ትልቅ መሣሪያ በመሆኑ የኢትዮ-ኮደርስ ፕሮጀክትም ለስኬቱ አጋዥ ነው። ይህን እውን ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ብቃት ያለው አመራር መስጠት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ኢትዮ ኮደርስ ስልጠናም ዘመኑን የዋጀ የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎትን በመዘርጋት የአሰራር ስርዓትን ለማዘመን ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። አገልግሎቱን ትልቅ መሠረተ ልማትን መገንባት ሳያስፈልግ በእጅ ባሉ ስልኮችና ኮምፒውተሮች ብቻ የዲጂታል እውቀትን በማዳበር ማህበረሰብን ማገልገል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ ሳይንስ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ በበኩላቸው ኢትዮ ኮደርስ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና ስላለው ቢሮው ይህን ለመተግበር እየሰራ ነው ብለዋል። ወጣቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የሥራ ባለቤት እንዲሆንና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልፀዋል። ለተግባራዊነቱም ክልሉ በሶስት ዓመታት ከ235ሺህ በላይ ዜጎችን ተሳታፊ ለማድረግ በየዓመቱ ከ58ሺህ በላይ ዜጎችን የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ህይወትና አኗኗር ከማቅለልና ዲጂታል ማህበረሰብን ከመፍጠር አኳያ ድርሻው ጉልህ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል(ዶ/ር) ናቸው። ያለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአንድ ሀገር ዕድገት ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮ-ኮደርስ ፕሮጀክት ዕቅድ እንዲሳካ የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የመንግስት ተጠሪዎች፣ ከንቲባዎችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በክልሉ የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳ ነው-አቶ ጥላሁን ከበደ
Apr 15, 2025 91
አርባ ምንጭ፤ሚያዚያ 7/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡ ክልል አቀፍ የኢትዮ-ኮደርስ ኢኒሼቲቭ አፈጻጸም ግምገማና ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፥ የቴክኖሎጂ ክህሎታቸው የዳበረ ዜጎችን መፍጠር የክልሉ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ ነው። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትኩረት ከተሰጣቸው ብዝሃ ዘርፎች አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን አስታውሰው፥ፕሮጀክቱ የብልጽግናን ራዕይ ለማሳካት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል። ሀገራት እድገት ያስመዘገቡት በቴክኖሎጂ ወደፊት በመሄዳቸው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ኋላቀርነትና ድህነትን ማስወገድ የምንችለው በቴክኖሎጂ የዳበረ ክህሎት ያላቸውን ዜጎች መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል። ኢትዮ ኮደርስ ዜጎችን በቴክኖሎጂ ክህሎት በማበልጸግ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከማድረግ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በር የሚከፍት ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል። የኮደርስ ስልጠና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም መንግስት ዜጎች ስልጠናውን በነፃ እንዲያገኙ ማመቻቸቱ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል። የክልሉ የኮደርስ ስልጠና አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ዜጎች ይህን ዕድል በመጠቀም ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ሊያራምዱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም የኢትዮ ኮደርስ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ለነገ የሀገር ተረካቢ ትውልድ የምንፈጥርበት ልዩ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። በክልሉ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት እስከ 60 ሺህ ዜጎችን በኮደርስ ለማሠልጠን ታቅዶ እስካሁን ድረስ 38 ሺህ ዜጎችን ማሠልጠን እንደተቻለ ተገልጿል። ከእነዚህም 6 ሺህ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት። አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ የድጋፍና ክትትል ስራውን በማጠናከር ለክልሉ የተሰጠውን ዕድል አሟጦ ለመጠቀም እንደሚሰራ ገልጸው፣ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንድወጡ ጠይቀዋል። በመድረኩ ላይ የኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።
ኢትዮጵያ በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው
Apr 14, 2025 97
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌደሬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የቴክኒክ ሙያ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት በመሆኑ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ክህሎት ላይ መሰረት ያደረገ እውቀት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የስራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማትን በማጠናከር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል። በኢትዮጵያ ለቴክኒክና ሞያ በተሰጠው ትኩረት በዘርፉ የሰለጠኑ በርካታ ሞያተኞች በኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት ምቹ ሆኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ አገራትም በቴክኒክ ሙያ ዘርፍ ያላቸውን የሰው ሀይል፣ እውቀት እና ልምድ በመለዋወጥና በጋራ በመስራት እርስ በእርስ መማማር እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ በአፍሪካ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ከሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሐመድ አብደል-አሊም በበኩላቸው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን በስድስት ዓመታት ውስጥ ከ13 በላይ አባል ሀገራትን ለማፍራት በቅቷል ብለዋል። የዌልዲንግ ዘርፍን በቀጣይ ለማሳደግ በሀገራት የኢንዱስትሪ ስትራቴጂዎችና በሙያ ትምህርት ስርዓቶች ውስጥ ማካተት እንደሚገባ አመልክተዋል። ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በሰው ሀይል ላይ ኢንቨስት ማድረግና የስልጠና መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል ። የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በበኩላቸው የዌልዲንግ ቴክኖሎጂ የዘመናዊ ኢንዱስትሪ መሰረት በመሆኑ ኢትዮጵያ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል አቋቁማ በርካታ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል። ዌልዲንግ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ የስራ እድል በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። የዌልዲንግ ሙያ የበለጠ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆን በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ሶስተኛው የአፍሪካ ዌልዲንግ ፌዴሬሽን ጉባኤና አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ እንድታካፍል እና ልምድ ልውውጥ እንድታደርግ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ናቸው ፡፡ 16 የአፍሪካ አገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ድረስ እንደሚቆይም ተገልጿል።
ቤላሩስ ለኢትዮጵያ በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ላይ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጥሪ ቀረበ
Apr 14, 2025 99
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ):- ቤላሩስ ለኢትዮጵያ በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ላይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክር እንድትቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ራይዜንኮቭ ከተመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት ልማትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ቤላሩስ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ እና ላሳየችው የገለልተኝነት አቋም ምስጋናቸውን አቅርበው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና በሌሎችም ዘርፎች በስፋት እየሰራችና አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ይገኛል ብለዋል። በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ከአጋር ሀገራት ጋር የምታደርገውን የትብብር ስራዎች ይበልጥ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ተወዳዳሪነትን በማጠናከር የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር በመሰረተ ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤትነት ላይ ስኬታማነትን እንድታረጋግጥ የአጋር ሀገራት ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት። የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ራይዜንኮቭ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራትና ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። በተለይም በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በማዕድን፣ በንግድ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ የሚቀርቡ የአጋርነት ፍላጎቶችን በመንተራስ በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ቤላሩስን እንዲጎበኙም ጋብዘዋል። የሁለትዮሽ ምክክሩ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከርና በተመረጡ ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያውያን ሀሳብ አፍላቂዎች በግዙፉ የቴክኖሎጂ ሁነት ላይ ስራቸውን ያቀርባሉ
Apr 14, 2025 116
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ግዙፉ የቴክኖሎጂ እና የጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች (ስታርትአፕ) ሁነት እንደሆነ የሚነገርለት 3ኛው ጂአይቴክስ አፍሪካ የቴክኖሎጂ መድረክ ዛሬ በሞሮኮ ማራካሽ ተጀምሯል። መድረኩ በአፍሪካ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ኢኖቬሽን እና የቢዝነስ ትስስር የመሪነት ስፍራ ላይ የተቀመጡ ተቋማት እና ግለሰቦችን ያገናኘ ነው። በሁነቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ130 ሀገራት በላይ የተወጣጡ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች፣ከ1 ሺህ 400 በላይ ስራቸውን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች፣ከ650 በላይ የመንግስት ተቋማት እና ከ350 በላይ ባለሀብቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ሳይበር ደህንነት፣ ትምህርት፣ ቴሌኮም፣ ፋይናንስ፣ ጤና፣ ስፖርት እና የግብርና ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች ከሚያቀርቧቸው የቴክኖሎጂ ስራ ፈጠራዎች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ። በአህጉራዊው የቴክኖሎጂ መድረክ የማህበረሰብን ችግር የሚፈቱ እና ህይወትን የሚያቀሉ ተጨባጭ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የቻሉ ኢትዮጵያውያንም ተሳታፊዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ በሁነቱ ላይ ስራቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ዘላቂ ልማት፣ ስራ ፈጠራ እና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ የጎንዮሽ ውይይቶች ይካሄዳሉ። የ2025 የጂአይቴክስ አፍሪካ መድረክ ለአፍሪካ ልማት እና ዲጂታል ሽግግር ትኩረት የሚሰጥ እና አፍሪካ የዓለም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ስራዎች ማዕከል ለማድረግ የሚሰራ ነው። በሞሮኮ ማራከሽ እየተካሄደ የሚገኘው መድረክም በአህጉሪቱ ያሉ ምርጥ አዕምሮዎችን በማሰባሰብ እና የእውቀት ሽግግር እንዲሳለጥ በማድረግ አፍሪካ በዓለም የቴክኖሎጂ ውድድር የመሪነቱን ቦታ እንድትይዝ አይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው ተብሎለታል። ዲጂታል ኢኮኖሚ ለአፍሪካ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ከ180 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ እና የአህጉሪቷ የሳይበር ደህንነት ገበያ በዓመት የ245 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል። ጂአይቴክስ አፍሪካ እስከ ሚያዚያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል። የቴክኖሎጂ ሁነቱ በሞሮኮ ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ የበላይ ጠባቂነት የሚመራ ነው።
ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል- ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
Apr 13, 2025 124
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2017(ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዲጂታል የአሰራር ስርዓትን በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል። ሚኒስትሩ የዘርፍ አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዲጂታላይዜሽንን በማስፋት እንዲሁም መሰረተ ልማቶች እንዲጠናከሩ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። ለአብነትም ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ 800 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በዲጂታል መንገድ መዘዋወሩን ጠቅሰው፤ ይህም በዲጂታል ስነምህዳር ውስጥ ትልቅ እመርታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል። የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በዚህም የኢንተርኔት እና የሞባይል ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍል እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በተያያዘም እስከ አሁን 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ምዝገባ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል። ይህም ከእቅዱ አንጻር መልካም የሚባል እና በቀጣዮቹ ጊዜያትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል። ከሰው ሀብት ልማት ጋር በተያያዘም በ5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እስከ አሁን 688 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተመዝግበው ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከነዚህም 270 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ማግኘታቸውን አመላክተዋል። ይህም ትልቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል። በአጠቃላይ ዲጂታል የአሰራር ስርዓት በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና የሁዋዌ ቴክፎርጉድ ግሎባል ውድድር አሸነፉ
Apr 12, 2025 185
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ቴክ ፎር ጉድ ግሎባል ውድድር አንደኛ በመውጣት አሸንፈዋል። በስድስት ተማሪዎች የተወከለው የኢትዮጵያ ቡድን ተማሪዎቹን ከአዲስ አበባ፣ ሃረማያ፣ ጅማ፣ ወልቂጤ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ያካተተ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በውድድሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፤ አርጀንቲና፣ አየርላንድ፣ ማላዊ፣ ቬትናም፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎችንም ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ ከተውጣጡ 12 ልዩ ቡድኖች ተወዳድረዋል። የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ግሎባል አምባሳደር የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ አሲያ ከሊፋም በዝግጅቱ በእንግድነት ተገኝታለች። ተማሪዎቹ የእንስሳትን ህመሞች አስቀድሞ ለመለየት በተዘጋጀውና በአርተፊሻል አስተውሎት በጎለበተው ኤርሊ ቬት (EarlyVet) በተሰኘው ፕሮጀክታቸው የተወዳደሩ ሲሆን በዚህም ትኩረት ለመሳብ ችለዋል። ፈጠራ ፕሮጀክቱ ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችበተለይም ግብ 2 "ዜሮ ርሃብ" እና ግብ 15 "ህይወት በምድር" ከሚለው ጋር የተጣጣመ መሆኑና በግብርና እና በእንስሳት ጤና ላይ ያሉ ወሳኝ ተግዳሮቶችን ይፈታል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል። የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ በቡድኑ ስኬት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ድሉ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ልዩ ችሎታ እና ፈጠራ የታየበት ነው ብለዋል። ሁዋዌ መጪው በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አመልክተዋል። ቡድኑ ለዓለም አቀፋዊ ውድድር እድል ያገኘው በግንቦት 2016 ዓ.ም በኤሳውራ ሞሮኮ በተካሄደው የክፍለ አህጉራዊ የቴክፎርጉድ (Tech4Good) ውድድር ወቅት ከ17 የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ 28 ቡድኖች ጋር ተወዳድሮ አንደኛ በወጣበት ወቅት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ2008 የተጀመረው የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ፕሮግራም በአገር ውስጥ ያለውን ውድድር ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጃል። ለተሳታፊ ተማሪዎች ከውድድር ባለፈ የሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት (AI)፣ ክላዉድ ኮምፒዉቲንግ፣5ኛ ትውልድ፣ ሳይበር ደህንነት እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ አጠቃላይ ስልጠና የሚወስዱበት እድል እንደሚያመቻች የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
ኮሌጁ ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት የአካባቢውን እንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እየደገፈ ነው
Apr 12, 2025 120
ደብረብርሀን፤ ሚያዚያ 4 / 2017(ኢዜአ) ፡-የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት በአካባቢው እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ። ኮሌጁ "ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሃሳብ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የጥናትና ምርምር ስራዎች ውድድር አካሄዷል። የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ባሻዬ በየነ እንደገለጹት የአገራችን ኢኮኖሚ የሚፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማምረት ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚጠበቅ ነው። በአሰልጣኞች፣ በሰልጣኞችና በኢንተርፕራይዞች ደረጃ የተካሄደው ቴክኖሎጂን የመቅዳት፣ የማላማድና የማሸጋገር ውድድር በቀጣይ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። ይህም ለአገራችን ኢኮኖሚ ውጤታማ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን በመለየትና እውቅና በመስጠት በቀጣይ ለህብረተሰብ ጥቅም እንዲውሉ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች እርስ በእርስ በመተዋወቅ፣ ተሞክሮ በመለዋወጥና በቅንጅት በመስራት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ እድልን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ህይወት አስናቀ እንደገለጹት ኤሌክትሪካል የወተት መናጫ ማሽን በመስራት ለውድድሩ መቅረባቸውን ተናግረዋል። ያቀረቡት ቴክኖሎጂም በ20 ደቂቃ ውስጥ ወተቱን በመናጥ ጥራት ያለው ቅቤ ለማምረት የሚያስችል ነው። የዌብ ዴቨሎፕመንትና ዳታ ቤዝ አድሚኒስትሬሽን ሰልጣኝ የሆነው ባየሁ ገበየሁ በበኩሉ ባለብዙ ልኬት የአፈር መመርመሪያና መረጃ ማከማቸት የሚችል ቴክኖሎጂ ይዞ በመቅረቡ ለአሸናፊነት መብቃቱን ተናግሯል። ቴክኖሎጂው የአፈሩን የማዕድን ዓይነት፣ ሙቀት፣ ርጥበትና አሲዳማነት በመለየትና መሬቱን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አስረድቷል። ከኢንተርፕራይዞች መካከልም አቶ ኢያሱ ገረመው እንደገለጸው ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ሸንብራና ጤፍን በቀን እስከ 200 ኩንታል መውቃት የሚችል ማሽን ለውድድር ይዞ መቅረቡን አስረድቷል። ከውጭ እስከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ይገባ የነበረውን የእህል መውቂያ ማሽን ከ400 ሺህ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ በመሆኑ አዋጭ ነው ብለዋል። በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተዘጋጀው የቴክኖሎጂ ውድድር ላይም በዞኑ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተወዳዳሪነት መሳተፋቸውም ተመላክቷል።
በማህበራዊ ሚዲያዎችና በኢንተርኔት ሊደርሱብን የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን እንዴት እንከላከል?
Apr 12, 2025 168
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 4/2017(ኢዜአ)፦በማህበራዊ ሚዲያዎችና በኢንተርኔት የሚፈጸሙ የማጭበርበር እንቅስቃሴዎች እየበረከቱ ይገኛሉ። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከዚህ ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉና ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያላቸውን ስጋቶች መከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስቀምጧል። የዲጂታል ማጭበርበሮችን ለመከላከል ልንወስዳቸው የሚገቡ የጥንቃቄ ርምጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርቧል፦ ያልታወቁ አድራሻዎችን ወይም ሊንኮችን ከመክፈት በመቆጠብ፤ ከላይ ያሉትን ወይም ተመሳሳይ አድራሻዎች በመልዕክት፣ በማህበራዊ መገናኛ፣ ወይም በሌላ መንገድ ከደረስዎ ከመክፈት መቆጠብ በተለይ “እንኳን ደስ ያለህ! ገንዘብ አሸንፈሃል፣ ይህን አገናኝ ጫን” የሚል መልዕክት ከመጣ፣ ይህ ማጭበርበሪያ ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ፤ የሞባይል እና የባንክ መረጃዎችን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በመጠቀም፤ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን ከታመኑ ምንጮች (እንደ Google Play) ወይም አፕስቶር (app-store) ብቻ ያውርዱ። የይለፍ-ቃልዎን ወይም የባንክ መለያዎችን ባልታወቁ ድረ-ገፆች ከማስገባት መቆጠብ፤ በዲጂታል ሚዲያዎች አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ ሪፖርት በማድረግ፤ እንደዚህ አይነት መልዕክቶች ወይም አድራሻዎች ካዩ፣ ወዲያውኑ ለEthio-CERT በኢ-ሜይል (ethiocert@insa.gov.et) ወይም በስልክ (933) ያሳውቁ፤ በነፃ Wi-Fi ስንጠቀም በጥንቃቄ በመጠቀም፤ በካፌዎች፣ በሆቴሎች፣ ወይም በሌሎች የህዝብ ቦታዎች ያለውን ነፃ Wi-Fi ሲጠቀሙ፣ የግል መረጃዎችን አያስገቡ።
ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ስነ ምህዳር ለመፍጠር ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ይገባል- አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ
Apr 12, 2025 124
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ስነ ምህዳር ለመፍጠር ዓለም አቀፍ ትብብር እና አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ። ኢትዮጵያ በብራዚል መዲና ብራዚሊያ በተካሄደው የብሪክስ የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ደህንነት እና ጥበቃ ስብሰባ ላይ ተሳትፋለች። በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ምህዳር ለመፍጠር ሀገር አቀፍ ትብብር እና ዓለም አቀፍ አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደሩ በስብሰባው ላይ ስለ ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ገለጻ አድርገዋል። ፖሊሲው የመንግስት፣ ህዝብ እና የበርካታ ባለድርሻ አካላት የጋራ ተሳትፎን ማዕከል ያደረገ፣ ለቁልፍ የመረጃ መሰረተ ልማቶች እና ለግል መረጃ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለዲጂታል የኢኮኖሚ ተግባራት ደህንነቱ የጠበቀ አሰራርን መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በአይሲቲ ደህንነት ዓለም አቀፍ ትብብር እና አጋርነት እንዲጠናከር ቁርጠኛ ናት ብለዋል። በብሪክስ ማዕቀፍ አማካኝነት የአይሲቲ ዘርፍ እድሎችን መጠቀም እና ስጋቶች በጋራ መከላከል እንደሚገባም ነው አምባሳደሩ ያሳሰቡት። ስብሰባው የብሪክስ አባል ሀገራት የአይሲቲ ደህንነት ይዞ የመጣቸው እድሎች እና ፈተናዎች ላይ ሀሳቦችን እንዲለዋወጡ እና ሀገራዊ ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡ ምቹ አጋጣሚን መፍጠሩ ተመላክቷል። አባል ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ ብሪክስ ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን በብራዚሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ጉባኤው የዌልዲንግ ሥራ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ለማስተዋወቅ ያስችላል
Apr 11, 2025 102
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ ሦስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ የዌልዲንግ ሥራ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ለማስተዋወቅና ግንዛቤን ለማሳደግ ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ። ሦስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 6 እስከ 8 በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል። በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰላሙ ይስሐቅ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ለጉባኤው ዝግጅቶች ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ16 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ40 በላይ የዌልዲንግ ክህሎት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ውድድር እንደሚካሄድም አንስተዋል፡፡ በዊልዲንግ ውድድሩ ከተለያዩ ክልሎች ተወዳድረው የተመለመሉ 21 ተወዳዳሪዎችን ኢትዮጵያ እንደምታሳትፍም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። በዌልዲንግ ላይ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፥ ጉባኤው ዌልዲንግን በተመለከተ ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ነው የጠቀሱት። ከዚህም በተጨማሪ ዌልዲንግ በኢንዱስትሪና በሌሎች ትልልቅ ዘርፎች እየተጫወተ ያለውን አበርክቶ ማስተዋወቅ ያስችላል ብለዋል፡፡ ልህቀት ማዕከሉ ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን በተጨማሪም ተኪ ቴክኖሎጂዎችን እያመረተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በሀገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ የዌልዲንግ ባለሙያዎችን በማፍራት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በማምረት በልማት ስራ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። ሶስተኛው የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጉባኤ "አፍሪካን ማብቃት፦ ለክልላዊ ውህደት እና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የዌልዲንግ አቅምን ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ኩባንያዎች፣ አምራቾች፣ ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ የአፍሪካ የዌልዲንግ ፌዴሬሽን 1ኛ ዓመታዊ ጉባኤን ግብጽ ያስተናገደች ሲሆን ናይጄሪያ ሁለተኛውን ጉባኤ ማዘጋጀቷ ይታወቃል፡።