ስፖርት
የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል
Apr 22, 2025 13
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ጨዋታውን ያካሂዳል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። ኢትዮጵያ መድን በ48 ነጥብ የአንደኝነት ደረጃውን ተቆናጧል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። መድን ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 ከፍ ያደርጋል። ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ለመራቅ ያስችለዋል። የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ምሽት 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል። ሃዋሳ ከተማ በ24 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ35 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተያያዘም ትናንት በተካሄዱ የ26ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ መቀሌ 70 እንደርታ 4 ለ 1 ፣ መቻል አዳማ ከተማን 2 ለ 0 እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል 
Apr 20, 2025 56
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ)፡- ወላይታ ድቻ በ46ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ያደርጋል። በሊቢያ ሚስራታ ከተማ የሚካሄደው ሻምፒዮና ትናንት ተጀምሯል። በሻምፒዮናው ላይ 25 የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ተሳታፊ ሆነዋል። ክለቦቹ በአራት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኢትዮጵያን ወክሎ በሻምፒዮናው የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ በምድብ ሶስት ከሞሪሺየሱ ኦሊምፒክ ዲ ኪዩርፓይፕ አሶሴሽን፣ ከሩዋንዳው ኪርሄ ቮሊቦል ክለብ፣ ከኬንያው ፕሪዝንስ ኬንያ፣ ከካሜሮኑ ፓድ ቮሊቦል ክለብ እና ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ተደልድሏል። ወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ከሊቢያው ኢትሃድ ትሪፖሊ ጋር ያደርጋል። 46ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና እስከ ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። ሻምፒዮናው በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን አስተናጋጅነት ይሚካሄድ ነው። እ.አ.አ በ1980 በተጀመረው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና የግብጹ አል አህሊ 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘዋል። የቱኒዚያ ስፋክሲያን ስድስት ጊዜ አሸናፊ ሲሆን የግብጹ ዛማሌክ እና የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ዋንጫውን ወስደዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል
Apr 19, 2025 56
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ወላይታ ድቻ ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። መርሃ ግብሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ከስሑል ሽሬ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል። ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ48 ነጥብ እየመራ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በ39 ነጥብ ይከተላል። ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ 37 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ሃዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን እና የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን በተመሳሳይ 10 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩ ነው። የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ እና የፋሲል ከነማው ጌታነህ ከበደ በተመሳሳይ 9 ጎሎችን በማስቆጠር ይከተላሉ።
ማንችስተር ዩናይትድ ሊዮንን ድራማዊ በሆነ ሁኔታ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ 
Apr 18, 2025 122
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017 (ኢዜአ)፦ በዩሮፓ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ሊዮንን 5 ለ 4 አሸንፏል። ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ በልብ አንጠልጣይ ክስተቶች የታጀበ ነበር። ማኑኤል ኡጋርቴ እና ዲዮጎ ዳሎት በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 መምራት ችሏል:: ኮረንቲን ቶሊሶ እና ኒኮላስ ታግሊያፊኮ ከእረፍት መልስ ከመረብ ላይ ያሳረፏቸው ግቦች ሊዮንን አቻ አድርገዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በመጠናቀቁ ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ አምርቷል። ራያን ቼርኪ በ105ኛው በጨዋታ እና አሌክሳንደር ላካዜት በ110ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ያስቆጠሯቸው ጎሎች ግብ ሊዮንን 4 ለ 2 መሪ አድርጎ ነበር። ይሁንና ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ114ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት፣ ኮቢ ሜይኖ በ120ኛው እና ሀሪ ማጓየር በ121ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ለማንችስተር ዩናይትድ ጣፋጭ ድል አስገኝቷል። የሊዮኑ ኮረንቲን ቶሊሶ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ውጤቱን ተከትሎ ማንችስተር ዩናይትድ በድምር ውጤት 7 ለ 6 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል። ማንችስተር ዩናይትድ በግማሽ ፍጻሜው ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ጋር ይጫወታል። አትሌቲኮ ቢልባኦ ሬንጀርስን በደርሶ መልስ ውጤት 2 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል። በሌሎች ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐርስ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን፣ ቦዶ ግሊምት ላዚዮን በድምር ውጤት በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል። ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ቦዶ ግሊምት በግማሽ ፍጻሜው ይገናኛሉ። የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በሚያዚያ ወር መጨረሻ ይካሄዳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም